ከ10 ሚሊየን ብር በላይ ጉቦ በመቀበል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉት የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ሰራተኞች ፍርድ ቤት ቀረቡ።

ሰራተኞቹ የግብር መጠንን በመቀነስ ከ10 ሚሊየን ብር በላይ ጉቦ በመቀበል ተጠርጥረው ነው በቁጥጥር ስር የዋሉት።

የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ ተረኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት የአዲስ አበባ ፖሊስ መርማሪ ያቀረበውን የጥርጣሬ መነሻንና የተጠርጣሪ ጠበቃ መከራከሪያ ነጥቦችን ተመልክቷል።

ችሎት ቀርበው ጉዳያቸው የታዩት ተጠርጣሪዎች ፦

➡ የአ/አ ገቢዎች ቢሮ ከፍተኛ ግብር ከፋዮች ቅ/ጽ/ቤት የታክስ ኦዲት ቡድን አስተባባሪ ሃብታሙ ግዲሳ፣

➡ የከፍተኛ ግብር ከፋዮች የታክስ ኦዲት ከፍተኛ ኦፊሰር ስምረት ገ/እግዚአብሔር፣

➡ የከፍተኛ ግብር ከፋዮች የታክስ ኦዲት ከፍተኛ ኦፊሰር ዮሴፍ ባቡ፣

➡ የከፍተኛ ግብር ከፋዮች ታክስ ኦዲት ከፍተኛ ኦፊሰር አቤኔዘር ቶሎሳ፣

➡ ከፍተኛ ግብር ከፋይ የታክስ ኦዲት ከፍተኛ ኦፊሰር ለሚ ሲሌ

➡ ገንዘብ ተቀባይ ባለሙያ ወ/ሮ መቅደስ አረጋዊ ናቸው።

ተጠርጣሪዎቹ የተሰጣቸውን የስራ ኃላፊነትን ወደ ጎን በመተው ከግብር ከፋይ ግለሰቦች ጋር በጥቅም በመመሳጠር ከግብር ከፋይ ድርጅቶች ” ግብር እንቀንስላችኋለን ” በማለት በመደራደር ከ100 ሚሊየን ብር የግብር መጠንን ወደ 13 ሚሊየን ብር ዝቅ በማድረግ ግብርን በመቀነስ ከተለያዩ ድርጅቶች በተለያዩ መጠኖች ከ10 ሚሊየን ብር በላይ ጉቦ ተቀብለዋል በማለት መርማሪ ፖሊስ የጥርጣሬ መነሻውን ለጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ አቅርቧል።

መርማሪ ፖሊስ በባንክ ሂሳባቸው የጉቦ ገንዘብ ገቢ የተደረገላቸው ተጠርጣሪዎች መኖራቸውን የሚያሳይ ማስረጃ መሰብሰቡን በማመላከት ተጨማሪ ግብረ አበር ለመያዝና ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ማስረጃዎች አሰባስቦ ለመቅረብ የ14 ቀን ጊዜ ቀጠሮ እንዲሰጠው ጠይቋል።

የተጠርጣሪዎቹ ጠበቃ በበኩሏ ደንበኞቿ በመርማሪ ፖሊስ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት ” አልፈጸሙም ” በማለት በመከራከር የዋስትና መብታቸው እንዲከበር ጠይቃለች።

መርማሪ ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹ በዋስ ቢወጡ ማስረጃ ሊያሸሹ ይችላሉ በማለት በጠበቃቸው የቀረበውን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ እንዲደረግ በመጠየቅ ተከራክሯል።

የፖሊስ የጥርጣሬ መነሻን እና ግራ ቀኙን ክርክር የመረመረው ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ የምርመራ መዝገቡ ጅምር በመሆኑ ተጨማሪ የምርመራ ማጣሪያ ጊዜ ለፖሊስ መስጠት አስፈላጊ መሆኑን በማመን የተጠርጣሪ የዋስትና ጥያቄን በማለፍ ለፖሊስ የ14 ቀን የምርመራ ማጣሪያ ጊዜ ቀጠሮ ፈቅዷል።

መረጃው የኤፍ ቢ ሲ ነው።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ፡– (@tikvahethiopia)