ከአፓርታይድ ማክተም 30 ዓመታት በኋላ ምን ውጤት ተገኘ?

የደቡብ አፍሪካ ጠቅላላ ምርጫ እየተቃረበ ነው። ከ20 ቀናት በኋላ ይከናወናል። ይህ ወቅት ከምርጫ በተጨማሪ ሀገሪቱ ከዘረኛው የአፓርታይድ አገዛዝ ጋር በይፋ መላቀቅ ከጀመረች 30ኛውን ዓመት ትደፍናለች። የቢቢሲዋ ጋዜጠኛ ኖማሳ ሜስኮ ከአፓርታይድ በኋላ በደቡብ አፍሪካ ያለውን ዴሞክራሲ እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ተከታዩን ዘገባ አዘጋጅታለች።

እሁድ መጋቢት 25/1986 – ልክ የዛሬ 30 ዓመት፣ እናቴ የያዘችውን የምርጫ ካርድ ወደ ድምጽ መስጫ ሳጥኑ ስታስገባ “ይህ ከእስር ቤት የምንወጣበት ካርድ” እንደሆነ ይሰማኛል አለችኝ። አቅሟ እንደጎለበተ ተሰምቷታል።

ያኔ የ43 ዓመት ሴት ነበረች። ልክ በሚሊዮን እንደሚቆጠሩ ደቡብ አፍሪካውያን እሷም ድምጽ ለመስጠት ስትቀርብ የመጀመሪያዋ ነበር።

ያ ወቅት ለ10 ዓመታት የዘለቀው የአነሳ ነጭ አመራርን ዘረኝነት፣ ጭቆና እና የከፋ ግፍ በጠመንጃ ለመጣል የሚደረገው ትግል ያበቃበት ነበር።

በዚህ ጊዜ ደምጽ ለመሰጥ አልበቃሁም ነበር – ዕድሜዬ ትንሽ ነበር። ሆኖም በምርጫ ቦታው ከመገኘት የከለከለኝ አልነበረም። ኧረ እንዳውም ጣቴ ላይ ድምጽ የሰጡ ሰዎችን ለመለየት የሚደረገውን ቀለም ቀብተውኝ ነበር።

ድምጽ መስጠቱ ለእናቴ ምን ማለት እንደነበር አይቻለሁ። ብዙኃን ጥቁሮች ነጻ መውጣታቸውን ብቻ ሳይሆን ከመራር ትግል በኋላ የራሳቸውን መንግሥት ለመምረጥ ዕድል አግኝተዋል።

ይህ የድምጽ መስጫ ቀን ከመድረሱ ጥቂት ቀናት በፊት ከፍተኛ ውጥረት ነበር።

ውጥረት ብቻ ሳይሆን ፖለቲካዊ ምክንያት ያዘሉ ሁከቶች ተበራክተው ነበር። እንኖርበት በነበረው ከጆሃንስበርግ በስተምስራቅ የምትገኘውን ካው ቲማ የአስለቃሽ ጭስ ሰማዩን ሸፍኖት ነበር።

በርካታ ብረት ለበስ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች ቀን እና ለሊት በተደጋጋሚ በቤታችን በኩል ያልፉ ነበር። ራቅ ብሎ ደግሞ የተኩስ ድምጽ ይሰማል።

ከታላቁ የምርጫ ዕለት አንድ ቀን ቀደም ብሎ እኔና ጓደኞቼ መንገድ ላይ እየተጫወትን ሳለ የናሽናል ፓርቲ ካናቴራ፣ ኳስ እና ሰንደቅ ዓለማ የሞላበት ነጭ የጭነት ተሽከርካሪ ባጠገባችን አለፈ።

ይህ ፓርቲ 1956 ዓ.ም ስልጣን ይዞ ለነጮች ያደላ እና ጨቋኝ የሆነውን የህግ መስመር ያሰመረ ነበር። ይህ መስመር አፓርታይድ ይባላል።

አብዛኞቻችን አዲስ ኳስ ኖሮን አያወቅም ነበር። ናሽናል ፓርቲ ኳሶች ሲሰጡን በጣም ደስ አለን። ደስታችን ግን ብዙ አልዘለቀም።

የጸረ አፓርታይድ ተቃዋሚዎች ሁሉንም ነገር ወሰዱብን። ካኔቴራዎቹን በእሳት አያያዟቸው። ኳሶቹን ደግሞ በሴንጢ ከጥቅም ውጪ አደረጓቸው።

“ከአሁን በኋላ ከጠላት ምንም ነገር እንዳትቀበሉ” ብለው ነገሩን። ከፍቶን ሊሆን ይችላል- ግን ለምን እንደሆነ ተረድተን ነበር።

የድምጽ መስጫ ዕለት ማለዳ በጣም ጸጥ ብሎ ነበር። ጸሃያማ ማለዳ ቢሆነም ፍርሃት እና ጭንቅት ነግሷል።

የድምጽ መሰጫ ጣቢያ ከኛ ቤት ፊት ለፊት በሚገኘው የመምህራን ኮሌጅ ነበር።

በርካታ ሰማያዊ እና ነጭ “የሰላም” ሰንደቅ ዓላማዎች ከፍ ብለው ይውለበለባሉ። የተለያዩ ቀለም ያላቸውን ልብሶች የለበሱ እና የፖለቲካ ፓርቲዎችን የሚወክሉ ሰዎች በየቤቱ ይዞራሉ። ነዋሪዎች ደምጽ እንዲሰጡ ያሳስባሉ።

ወጣቶች እና አዛውንቶች የተሰለፉባቸው ረዣዥም ሰልፎች ይታያሉ። እጃቸውን ወደ ላይ ከፍ አድርገው “ሲኩሉሌኪሌ – ነጻ ነን” እያሉ ያዜማሉ።

እኔ ግን የሚሰማኝ ተቃራኒው ነው። ፈረስ ላይ የተቀመጡ ነጭ የፖሊስ መኮንኖች በአጠገባችን ሲመላለሱ መደበቅ ያሰኘናል።

አሁንም ድረስ የአፓርታይድ ፖሊሶች ይጠቀሙባቸው የነበሩ አነፍናፊ የጀርመን ሼፐርድ ውሾችን እፈራለሁ። አንዳንዴ ያለምንም ምክንያት እኛ ህጻናት ላይ ይለቋቸው ነበር።

ሆኖም በዚያ መንደር ለነጻነት የተደረገውን ትግል የሚያስታውሱ በርካታ መልካም ማስታወሾች አሉ። ሰለዚያ በዚህ መንደር የቱሪስት መህብ ተቋቁሟል።

በታዋቂው ቪላካዚ መንገድ ላይ በአንድ ወቅት ፕሬዝዳንት የነበሩት ኔልሰን ማንዴላ እና ሊቀ ጳጳሱ ዴዝሞንድ ቱቱ ኖረውበት የነበረ ሆቴል ይገኛል።

የዚህ ሆቴል ባለቤት ሳኩማዚ ማኩቡላ “ቪላካዚ መንገድን ቱሪዝም በጣም ጠቅሞታል። ተሪስቶች ደቡብ አፍሪካ እንዴት እዚህ እንደደረሰች እየተመላለሱ ሲመለከቱ አስተውል ነበር። ከዚያ እዚህ መንገድ ላይ ምግብ ለመሸጥ ወሰንኩ” ይላሉ።

ማኩቡላ ባለፉት ሶስት አስርት ዓመታት ለነበሩት መንግሥታት በራሳቸው ጥረት ድጋፍ ሲያደረጉ እንደቆዩ ይገልጻሉ።

“ያለፉት 30 ዓመታት ለመንግሥታችን የሙከራ እና የስህተት ጊዜ ነበሩ። እየተማሩ እንደነበር ማወቅ አለብን። እዚህ 500 የስራ ዕድል ፈጥሬያለሁ። በደምብ ነው የምተኛው ምክንያቱም የኔ ጥረት ልዩነት እንደፈጠረ አውቃለሁ” ሲሉም አክለዋል።

ከነጻነት በኋላ የመጀመሪያዎቹ ዓመታት ከማንዴላ የመጀመሪያ የስልጣን ዘመን ወዲህ የነበረው ዲሞክራሲ ተስፋ ሰጪ ነበር። ታቦ ምቤኪ ሁለተኛውን ስልጣን ሲቆጣጠሩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጀቶች እና የመናገር እንዲሁም የፕሬስ ነጻነት አብቧል።

አሁን ግን በርካቶች ያ መልካም ዘመን እንዳከተመለት ይሰማቸዋል። አሁንም ድረስ በስልጣን ላይ ያለው ኤኤንሲ ፓርቲ በሙስናና በውስጣዊ ሽኩቻ ስሙ መነሳት ከጀመረ ቆይቷል።

በደቡብ አፍሪካ የስራ አጦች ቁጥር ጣራ ነክቷል። ወንጀል ተበራክቷል። በርካቶች አሁንም እንደ ኤሌክትሪክና ውሃ ያሉ መሰረታዊ አገልግሎቶችን ለማግኘት ይቸገራሉ።

ማኩቡላ ያሳለፉት እና ውሳጣቸው ያለው የዲሞክራሲ መንፈስ በቪላካዚያ መንገድ አይገኝም።

ቪላካዚያ ከኬፕታውን የ10 ደቂቃ የመኪና መንገድ ርቀት አለው። በስፍራው ተንቀሳቃሽ መጸዳጃ ቤቶች ተደርድረው ይገኛሉ። እነዚህ መጸዳጃ ቤቶች ከጽዳት ጋር አይተዋወቁም።

በአካባቢው ትምህርት ቤት የለም። በርካታ ኢ-መደበኛ ቤቶች ይገኛሉ። ወጣት እናቶች ከኑሮ ጋር እጅግ የሚታገሉበት ቦታ ነው።

የአከባቢው ነዋሪዋ ታስኒማ ሲልቬስተር “የ30 ዓመታት ዲሞክራሲ ለኔ ምንም ነው። ምንም የማከብረው የምደስትበት ነገር የለም” ብላለች።

የ38 ዓመቷ ሴት ቀጥላም “በዚህ ዓመት ድምጽ ለመሰጠት ብዙም አልጨነቅም። ምክንያቱም ኤኤንሲ ሰራሁት የሚለውን ነገር በሙሉ አላየሁትም። ስራ የለኝም፣ ንጹህ የመጠጥ ውሃ የለንም፣ መጸዳጃ የለም። ብስጩ እና ተስፋ የቆረጠ ሰው ሆኛለሁ” ስትል ተናግራለች።

የዚህ እናት ታሪክ በመላው ደቡብ አፍሪካ የብዙ ዜጎችን ህይወት የሚያንጸባርቅ ነው። ዛሬ በደቡብ አፍሪካ ባጣ በነጣው እና በናጠጠው ሃብታም መካከል ያለው ልዩነት እጅግ ሰፍቷል።

በክሊፕቶን የሚኖሩ ነዋሪዎች በነጻነት ትግል ውስጥ ያላቸው ቦታ እንደተዘነጋ ያስባሉ። የ1946 ዓ.ም የነጻነት ቻርተር የተፈረመው እዚያ ነው። ቻርተሩ አፓርታይድን የሚታገሉ ሰዎች ለዲሞክራሲያዊት ደቡብ አፍሪካ ያላቸውን የሩቅ ተስፋ ያሰፈሩበት ነበር።

ይህ ታሪካዊ ቻርተር በተፈረመበት ቦታ የቱሪስት አስጎብኚ ሆኖ የሚሰራው ናትኮዞ ዱቤ “ችላ ከተባልን ብዙ ጊዜ ተቆጥሯል። በነጻነት ቻርተሩ ላይ የተቀመጡት አስር ነገሮች አንዱም አለመተግበሩ ያሳዝናል” ሲል ተናግሯል።

የፖለቲካ ተንታኙ ቴሳ ዱምስ ያለፉትን 30 ዓመታት መገምገም ከባድ ነው ትላለች።

“የሀገራችን መሰረታዊ ሁኔታ ተቀይሯል ብለው ብዙ ሰዎች እንደማያስቡ ግልጽ ነው” ስትል ታስረዳለች።

“ካለፈው ጊዜ ጋር የሚመሳሰሉ በርካታ ነገሮች አሁንም አሉ. . . እኩልነት ከፍ ባለ ደረጃ ተዛብቷል። እንዲያውም በዲሞክራሲው ዘመን ጨምሯል” ስትል አክላለች።

በደቡብ አፍሪካ በመቶዎች የሚቀጠሩ የሰለጠኑ ሃኪሞች በበርካታ ከተሞች ለተቃውሞ ውጥተዋል። ምክንያቱም ስራ ማግኘት አዳጋች ሆኖባቸዋል።

ዶክተር ሙቱማዝ ኤመርን ቶማስ ከተመረቀችበት ስራ ጋር በማይገናኝ ስራ ላይ ተሰማርታለች።

“በጣም ተስፋ አስቆራጭ ነው። ምክንያቱም የደቡብ አፍሪካ ህዝብ በቂ የጤና አገልግሎት እያገኘ አይደለም። እየወደቀ ያለ ስርዓት ነው ያለን። ለዚያ ነው 800 ብቁ የሆንን ዶክተሮች ስራ አጥተን ቤት የተቀመጥነው” በማለት ትገልጻለች።

በተለይ ወጣቶች ለውጥ እየጠየቁ ነው። ኤኤንሲ ያመጣዋል ብለው ያሰቡት ዴሞክራሲ እና ፓርቲው ላይ ያላቸው ተስፋ እና እምነት ሊሟጠጥ ይችላል።

በሁሉም ነገር ተስፋ ቆርጠው ራሳቸውን ከምርጫው ለማራቅ የወሰኑም አሉ።

ሆኖም ልክ እንደኔ እናት በአፓርታይድ ውስጥ ያሉ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ ይህንን ድል ለአፍታም ሊዘነጉት አይችሉም። አሁንም ድረስ የድምጽ መስጫ ወረቀት ከፍተኛ ኃይል እንዳለው ያምናሉ።

በዲሞክራሲያዊ አስተዳደር ውስጥ ግንቦት 21/2016 በሚደረገው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ እኔ ለስራ እሰማራለሁ። ስለዚህ እናቴ 1986 ከእኔ ጋ በተገኘችበት በተመሳሳይ ቦታ ማለትም ካዋ ታህማ ድምጽ መስጫ ጣቢያ የ6 ዓመት ልጇን ይዛ ልትገኝ ቀጠሮ ይዛለች።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ ( ቢቢሲ ዜና )