ከሰሞኑን በማህበራዊ ሚዲያዎች አንድ አባት  በጎረምሶች ተከበው ሲመቱ ፣ ሲሰደቡ ፣ ሲዘለፉ ፣ ሲዋከቡ በቪድዮ ታይቷል።

ይህን እጅግ አሳፋሪና በምን አይነት ሁኔታ ላይ እንዳለን ሚያሳይ ቪዲዮ ያጋሩት ደግሞ እራሳቸው የድርጊቱ ፈጻሚዎች ናቸው።

ድርጊቱ ብዙዎችን ክፉኛ አስቆጥቷል። በርካቶች ስለ ነገ በማሳብ ፍርሃት ውስጥ ከቷቸዋል።

በእርግጥ በሀገራችን ያላየነው ግፍ ፣ ያልሰማነው ክፉ ተግባርና ጭካኔ ምን አለ ? እንዘርዝር ብንልስ ቦታው፣ ጊዜው  ይበቃናል ? በፍጹም !

ከዚህ በፊትም እንደምንለው በቪዲዮዎች ተቀርጾ የምናየው ምናልባትእድለኞች ሆነን ከብዙ አንዱ እንጂ ስንት ያላየነው ይኖራል።

ወደ ቪድዮው ስንመለስ ተከበው ሲመቱ፣ ሲዋከቡ ፣ ሲዘለፉ የነበሩት አባት ‘ እንጀራ ፍለጋ እግር ጥሏቸው እንደመጡ ‘ ይገልጻሉ የሚጠይቀን የለም ባዮች ጎረምሶች ‘ እዚህ አካባቢ ምን ትሰራለህ ? ለምን እዚህ መጣህ ? ከመጣህበት ቦታስ እንጀራ የለም ? ‘ ሲሉ እጅግ በንቀት ያዋክቧቸዋል።

ይህን ተግባራቸውን እንደ በጎ ስራ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ አጋርተውታል።

የትኛውም ዜጋ በገዛ ሀገሩ የመንቀሳቀስ መብት አለው ? ካልሆነ ስለምን #ኢትዮጵያዊ ይባላል ? ጥፋት ካለበት ፣ ከተጠረጠረ የሚጠይቀው ህግ እንጂ የሰፈር ጎረምሳ አይደለም። ግለሰቦቹ ጥርጣሬ አለን ካሉ ህግን ማሳወቅ እንጂ ማነው ፤ የትኛው ህግ ነው ይህንን መብት የሰጣቸው ? 

ይህ ተግባር በተለይ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ እየተነዛ ያለው የጥላቻ ስብከት ምን ያህል ስር እንደሰደደ እንደሆነ ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ሲሆን ነገን እጅግ አስፈሪ ያደርገዋል።

ግልጽ የሆነ የብሄርና የግለሰቦች ጥላቻ ፣ ልብም አእምሮም በጥላቻ መሞላት፣ አይንም በጥላቻ መታወር ፦

– ሌላው ይቅር ታላላቆቻችን እንዳናከብር

– ለእምነታችን ፣ ለሃይማኖታችን ቦታ እንዳይኖረን

– ለሰው ልጅ ትንሽ እንኳን ቦታ እንዳንሰጥ

– ለህግ እና ስርዓት ቅንጣት ታክል ደንታ እንዳይኖረን

– ባህል፣ ወግ ፣ አብሮነት ለሚባለው ጉዳይ ቦታ እንደሌለን

– ነገ እኔስ ምን ይገጥመኛል ? ምን እሆን ይሆን ? በህይወት አጋጣሚ የት እሄዳለሁ ፣ ምን አካባቢ እገኛለሁ የሚለውን ለማገናዘብ እንኳን እንዳንችል ያደርገናል።

ሰዎች ወደው ሳይሆን በስርዓት፣ በግለሰቦች፣ በአንቂዎች ፣ በሚዲያዎች… አማካኝነት ነው ጥላቻ እንዲውጣቸው እና ማገናዘብ ፣ ቆም ብሎ ማሰብ የሚባለውን መሰረታዊ ነገር እንዲያጡት የሚሆነው።

ሰዎች ከመሰል ድርጊታቸው እንዲታቀቡ አብሮነት ፣ ፍቅር ፣ መግባባት፣ መከባበር ፣ ህግ ፣ ስርዓት፣ ወንድማማችንነትን ከማስተማር ባለፈ በህግ ማረም ፣ ነገ መዘዙ የከፋ እየሆነ ስለሚሄድ ከወዲሁ እንዲገታ በአንድ ላይ ማውገዝ ፣ ተበዳይን መካስ ፣ እውነት ህግ የበላይ ነው የምንል ከሆነም ለራሳችን ስንል ህግን ሁሌም ማስከበር ነው።

ዛሬ ላይ እንዲህ ያሉና ከዚህ ቀደምም በየሀገሪቱ ክፍሎች የሰማናቸው ፍጹም አደገኛ የሚባሉ ጉዳዮች የሳምንት አጀንዳ እየሆኑ እያለፉ ይመስለን ይሆናል ግን በእርግጠኝነት መዘዛቸው የከፋ ሊሆን ይችላል።

ውጤታቸው ዛሬ ሳይሆን ውሎ አድሮ ምናልባትም አመታትን አልፎ ይታይ ይሆናል ስለሆነም እናስብበት ! ትውልዱን ከስህተቱ እናርመው ፤ ወገኑን እንዲጠላ ሳይሆን እንዲወድ ፣ እንዲያከብር እናስተምረው።

በሁሉም ዘንድ አውቀናል ታውቀናል ፣ ዛሬ ስልጣን አለን፣ ሚዲያውም የኛው ነው የምንል ሰዎችም ‘ አይ የኔ ወገን ስለሆነ ፍጹም ጻዲቅ ነው ፣ አይሳሳትም ፣ ጀግና ነው ፣ ቢሳሳትም ምንም ችግር የለውም እኔ እከላከልለታለሁ ‘ ከሚል አደገኛ እና ብዙ መዘዘ ካለው አመለካከት መራቅ ይገባናል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ ፡-(@tikvahethiopia)