እየተስፋፋ ባለው አዲሱ የኮቪድ ዝርያ በርካቶች እየተያዙ መሆናቸውን ሳይንቲስቶች ገለጹ…….

በቅርቡ በዋነኝነት ሊስፋፋ በሚችል አዲስ የኮቪድ ዝርያ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን ሳይንቲስቶች ገለጹ።

በሰኔ ወር ጀርመን ውስጥ የተገኘው ኤክስኢሲ የተሰባለው ዝርያ በዩናይትድ ኪንግደም፣ ዩናይትድ ስቴትስ፣ ዴንማርክ እና በሌሎች በርካታ አገራት ውስጥ መከሰቱ ተገልጿል።

ምንም እንኳን ክትባቶች ከባድ ጉዳት እንዳይደረስ ለመከላከል የሚረዱ ቢሆኑም፣ አንዳንድ አዳዲስ ዝርያዎች በመጪው ክረምት ወራት ዝርያው እንዲሠራጭ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

በኮቪድ በጠና የመታመም ዕድል ላላቸው ሰዎች የዩናይትድ ኪንግደም ብሔራዊ የጤና አገልግሎት (ኤንኤችኤስ) ከዚህ ቀደም ለተከተቡ በነጻ የማጠናከሪያ ክትባት ይሰጣል ተብሏል።

ክትባቶቹ የኦሚክሮን ዝርያዎችን ለመከላከል እንዲያስችሉ ሆነው ቢሻሻሉም፣ ለአዲሱ ዝርያ ኤክስኢሲ በሚል ተደረገ ማሻሻያ አለመኖሩ ታውቋል።

በለንደን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የጄኔቲክስ ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር የሆኑት ፕሮፌሰር ፍራንሷ ባሎው ለቢቢሲ እንደተናገሩት ምንም እንኳን ኤክስኢሲ ከሌሎች የቅርብ ጊዜ የኮቪድ ዝርያዎች “በመጠኑ ከፍ ያለ የመተላለፍ አቅም” ቢኖረውም እየተሰጡ ያሉት ክትባቶች አሁንም ጥሩ መከላከያ ይሆናሉ።

ኤክስኢሲ በቀዝቃዛ ወራት በዋነኝነት የሚሠራጨው የኮቪድ ዝርያ ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል።

“ኃላፊነት መውሰድ”

በካሊፎርኒያ የሚገኘው የስክሪፕስ ሪሰርች ተቋም ዳይሬክተር የሆኑት ኤሪክ ቶፖል ኤክስኢሲ “ገና መሠራጨት እየጀመረ ነው” ብለዋል።

“በበሽታው መያዝ እና በስፋት የሚሠራጭበት ማዕበል ከመጀመሩ በፊት ብዙ ሳምንታት ወይም ሁለት ወራትን ይወስዳል” ሲሉ ለኤልኤ ታይምስ ተናግረዋል።

“በእርግጠኝነት ኤክስኢሲ የበላይነቱን እየወሰደ ነው። ይህ ቀጣዩ ዝርያ ይመስላል።ወደ ከፍተኛ ደረጃዎች ለመድረስ ግን ወራት ያስፈልጉታል” ብለዋል።

የኤክስኢሲ ኮቪድ ምልክቶች ምንድን ናቸው?

ምልክቶቹ ከብርድ ወይም ከጉንፋን ጋር ተመሳሳይ ናቸው ተብሎ ይታሰባል፡-

  • ከፍተኛ ሙቀት
  • ህመም
  • ድካም
  • ሳል ወይም የጉሮሮ መቁሰል

ብዙ ሰዎች ከኮቪድ ስሜት በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ሊሻላቸው ቢችልም ለማገገም ግን ብዙ ጊዜ ሊወስድባቸው ይችላል።

በዴንማርክ እና በጀርመን ኤክስኢሲ “ጠንካራ ሥርጭት” አሳይቷል ሲሉ የኮቪድ መረጃ ተንታኝ የሆኑት ማይክ ሃኒ በኤክስ ማኅበራዊ ትስስር ላይ ገልጸዋል።

ከበፊቱ ያነሰ ምርመራ በመኖሩ ምክንያት ምን ያህል የኮቪድ ሥርጭት እንዳለ ለማወቅ አስቸጋሪ ያደርገዋል።

የዩናይትድ ኪንግደም የጤና ጥበቃ ኤጀንሲ (ዩኬኤችኤስኤ) የቫይረሶች መለዋወጥ የተለመደ ነገር ነው ብሏል።

ለነጻ ማበረታቻ ክትባት ብቁ የሆኑ ሰዎች የሚከተሉትን የሚያካትቱ ናቸው፡

  • ዕድሜያቸው ከ65 ዓመት በላይ የሆኑ አዋቂዎች
  • በአረጋውያን እንክብካቤ መስጫ ውስጥ የሚኖሩ
  • ከስድስት ወር በላይ የሆነው የጤና ስጋት ያለባቸው
  • የጤና አገለግሎት ባለሙያዎች፣ ድጋፍ ሰጪዎች እና የማኅበራዊ እንክብካቤ ሠራተኞች ናቸው።

ለጉንፋን እና ለኮቪድ የሚሰጠው ዋናው ክትባት በጥቅምት ወር ይጀምራል። አንዳንዶች ግን ቀደም ብለው ክትባቶቻቸውን ሊያገኙ ይችላሉ ተብሏል ።

የዩኬኤችኤስኤ ምክትል ዳይሬክተር ዶ/ር ጋይትሪ አሚርታሊንግም እንዳሉት “ቫይረሶች በጊዜ ሂደት መለወጣቸው የተለመደ እና የሚጠበቅ ነው። በዩናይትድ ኪንግደም እና በዓለም አቀፍ ደረጃ እየመጡ ካሉ የኮቪድ ዝርያዎች ጋር የተያያዙ ሁሉንም መረጃዎችን መከታተልን እና መረጃን በመደበኛነት ማሳወቅ እንቀጥላለን” ብለዋል።

“በኮቪድ-19 የሚከሰተውን ከባድ በሽታ ለመከላከል ክትባት መከላከያ ይሰጣል። በብሔራዊው የጤና አገልግሎት ጥሪ የሚቀርብላቸው በሙሉ ክትባታቸውን እንዲወስዱ እናሳስባለን” ሲሉ ጥሪ አቀርበዋል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ፡– (ቢቢሲ)