አዲሱ የሕዝብ በዓላት እና የበዓላት አከባበር ረቂቅ አዋጅ ግንቦት 20ን ያስቀረዋል?

ላለፉት 49 ዓመታት በሥራ ላይ የቆየው የሕዝብ በዓላትን እና የእረፍት ቀንን ለመወሰን የወጣ አዋጅ በአዲስ ሊተካ ረቂቅ ተዘጋጅቶለታል። የሚኒስትሮች ምክር ቤት ታኅሣሥ ወር ላይ ባደረገው ስብሰባ ረቂቅ አዋጁን አጽድቆ ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መርቶታል።

ዛሬ የመጨረሻ መደበኛ ስብሰባውን አድርጎ ለአንድ ወር እረፍት የተበተነው ፓርላማው፤ መጋቢት ወር ላይ ወደ ሥራ ሲመለስ ይመለከታቸዋል ተብሎ ከሚጠበቁ አዋጆች መካከል ይህ የሕዝብ በዓላትን የሚደነግግ ረቂቅ አዋጅ ይገኝበታል።

የሕዝብ በዓላትን ለመወሰን ወደ ፓርላማ የተመራው ይህ ረቂቅ፤ ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተደደር ደርግ በ1967 ዓ.ም ያወጣውን አዋጅ እና ኢህአዴግ በ1988 ዓ.ም. ያደረገውን ማሻሻያ የሚሽር ነው።

በአሁኑ ወቅት በሥራ ላይ ያለው በደርግ መንግሥት የወጣው አዋጅ 13 የሕዝብ እና ሃይማኖታዊ በዓላትን በብሔራዊ ደረጃ እንዲከበሩ የደነገገ ነበር። ከእነዚህ ውስጥ አሁን የማይከበሩት የመስከረም 2 የአብዮት በዓል (ሕዝብ ንቅናቄ/ሬቮሉሽን) መታሰቢያ” እና መስከረም 1 የተወሰነለት “ኤርትራ ከእናት አገሯ ከኢትዮጵያ ጋር የተዋሃደችበት ዕለት” ይገኙበታል።

ኢህአዴግ ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ በዚህ አዋጅ ከተዘረዘሩት በዓላት ውስጥ የድል ቀን ላይ ብቻ ማሻሻያ በማድረግ ይሄንን አዋጅ መተግበር ቀጥሏል። የሕግ ባለሙያ እና ጠበቃ አቶ አንዱዓለም በእውቀቱ እንደሚያስረዱት፣ ይህ ማሻሻያ የድል (የአርበኞች) ቀንን በፊት ይከበርበት ከነበረው መጋቢት 28 ወደ ሚያዝያ 27 ቀን የቀየረ ነው።

አሁን በሥራ ላይ ባለው አዋጅ እና በአተገባበሩ ላይ ክፍተቶች እንዳለ ለቢቢሲ የተናገሩት አቶ አንዱዓለም፤ በሕጉ ላይ የተቀመጠው የሕዝብ ንቅናቄ (ሬቮሉሽን) ቀን በሌላ አዋጅ ሳይሻር መንግሥት ቀኑን ማክበር ማቆሙን አስታውሰዋል።

“ኤርትራ ከእናት አገሯ ኢትዮጵያ ጋር የተዋሃደችበት ቀን ተብሎ ከዘመን መለወጫ ቀን ጋር አንድ ላይ ይከበር ነበረ። . . . ኤርትራ ከዚያ ወዲህ ተገንጥላ፣ ራሷን አገር ሆና እየኖረች ያለች አገር ነች። በአዋጅ ግን ይሄንን አላስቀረነውም” ሲሉ የሕግ ባለሙያው የተመለከተቱትን ሌላ ክፍተት ጠቅሰዋል።

ለአዲስ ረቂቅ አዋጅ የተዘጋጀው ማብራሪያም የቀድሞው አዋጅ “የበዓላቱን የአከባበር ሁኔታ በዝርዝር ያልደነገገ” መሆኑን ያገልጻል። ማብራሪያው፤ “[አዋጁ በዓላቱ] የሚከበሩበትን ሁኔታ በግልጽ ያልደነገገ በመሆኑ የበዓላቱ አከባበር በሚፈለገው ልክ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጎልቶተው እየወጡ እና እየታወቁ እንዲሁም ሊያስገኙ የሚችሉትን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እያስገኙ ነው ለማለት አያስደፍርም” ሲል አዋጁን ለማሻሻል ምክንያት ያለውን ጉዳይ ያስረዳል።

አዲሱ ረቂቅ አዋጅ ያመጣቸው ለውጦች

በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት እና በፍትህ ሚኒስቴር ውሳኔ መሠረት የተዘጋጀው አዲሱ ረቂቅ አዋጅ፤ ከቀድሞው አዋጅ የሚለየው ዋነኛ ጉዳይ የበዓላት አከባበርን በተመለከተ ዝርዝር ሁኔታዎችን የያዘ መሆኑ ነው።

በረቂቅ አዋጁ የሕዝብ በዓላትን “ተከብረው የሚውሉ ብሔራዊ በዓላት”፣ “ታስበው የሚውሉ ብሔራዊ በዓላት” እና “ሃይማኖታዊ በዓላት” ሲል ይከፋፍላቸዋል።

ተከብረው የሚውሉ ብሔራዊ በዓላት መደበኛ ሥራ ዝግ የሚሆንባቸው ቀናት እንደሆነ በረቂቁ ላይ ሰፍሯል። በዚህ ዝርዝር ውስጥ የሚገኙ በዓላት የዘመን መለወጫ (እንቁጣጣሽ)፣ የአድዋ ድል፣ የሠራተኞች (ላብአደሮች) ቀን እንዲሁም የአርበኞች (የድል) ቀን ናቸው።

ሥራ ሳይዘጋ በተለያዩ ሥነ ሥርዓቶች ታስበው የሚውሉ ብሔራዊ በዓላት ደግሞ ሁለት ሲሆኑ፣ የካቲት 12 ቀን የሚከበረው የሰማዕታት ቀን፣ ኅዳር 29 ቀን የሚከበረው የኢትዮጵያ ህብረ-ብሔራዊነት (የብሔር ብሔረሰቦች) ቀን ነው። የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ከ1998 ዓ.ም. ጀምሮ ላለፉት 18 ዓመታት ሲከበር የቆየ ቢሆንም በሥራ ላይ ባለው የሕዝብ በዓላት እና የእረፍት ቀናት አዋጅ ላይ የተደነገገ አልነበረም።

ወደ ምክር ቤቱ የተላከው ረቂቅ ላይ በሃይማኖታዊ በዓልነት የተቀመጡት አምስት የክርስትና እንዲሁም ሦስት የእስልምና እምነት በዓላት ሲሆኑ፣ ከዚህ ቀደም ከነበረው ዝርዝር ውስጥ የተደረገ ለውጥ የለም።

በረቂቁ ላይ የተቀመጡት የእስልምና እምነት በዓላት የኢድ-አልአድሃ (አረፋ)፣ የመውሊድ በዓል እና የኢድ-አልፈጥር በዓላት ናቸው። መስቀል፣ ገና (ልደት)፣ ጥምቀት፣ ስቅለት እና ትንሳኤ (ፋሲካ) ደግሞ በዚህ ዝርዝር ውስጥ የተካተቱ የክርስትና እምነት በዓላት ናቸው።

በረቂቁ ላይ የተቀመጡት በዓላት በሙሉ በውጭ አገር የሚገኝ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ወይም ቆንስላ ውስጥም “ታሪካዊ እና ሃይማኖታዊ ሥርዓታቸውን በጠበቀ ሁኔታ” እንደሚከበሩ አስቀምጧል። የረቂቁ ማብራሪያ እንደሚያስረዳው ይህ የሚደረገው “የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች እና ቆንስላዎች የኢትዮጵያ የግዛት አካል ተደርገው የሚወሰዱ” በመሆናቸው ነው።

ረቂቅ አዋጁ ሁሉም ብሔራዊ በዓላት የሚከበሩበትን ሁኔታ ያስቀመጠ ሲሆን፣ ከዘመን መለወጫ እና ከአርበኞች (የድል ቀን) በዓላት ውጪ ላሉት የሕዝብ በዓላት አከባበራቸውን የሚያስተባብር የፌደራል መንግሥት መሥሪያ ቤት መድቧል።

የአድዋ የድል በዓልን አከባባር “በባለቤትነት የማስተባባር” ኃላፊነት የተሰጠው ለመከላከያ ሚኒስቴር ነው። ሌሎቹ የሕዝብ በዓላት አከባበር ላይ ባልተጠቀሰ መልኩ የአድዋ ድል ሲከበር “የበዓሉ አከባበር በሁሉም የመንግሥት እና የግል የመገናኛ ብዙኃን ሽፋን ተሰጥቶት እንዲዘገብ” እንደሚደረግ ረቂቁ ላይ ተቀምጧል።

የዓለም የሠራተኞች ቀን “የሠራተኞችን ጉዳይ በሚመራው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት አስተባባሪነት” እንደሚከበር በረቂቁ ላይ ሰፍሯል። የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር ደግሞ የካቲት 12 የሚታሰበውን የሰማዕታት ቀን በዓል የማስተባበር ኃላፊነት ተጥሎበታል።

በዚህ ረቂቅ ላይ ለመጀሪያ ጊዜ በሕዝብ በዓላት ዝርዝር ውስጥ የገባውን የኢትዮጵያ ህብረ ብሔራዊነት (የብሔር ብሔረሰቦች) ቀን በዓልን የማስተባበር ኃላፊነት የተሰጠው ደግሞ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ነው።

ግንቦት 20 ቀረ?

የደርግ መንግሥት ወድቆ ኢህአዴግ ሥልጣኑን የተቆጣጠረበት ግንቦት 20፤ የተለይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስተዳደር ወደ ሥልጣን ከመምጣቱ በፊት ለአስርት ዓመታት በድምቀት ሲከበር ቆይቷል። ቀኑ ሲከበርም ሥራ እና ትምህርት ዝግ ይሆኑ ነበር።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ግን የበዓሉ አከባበር የቀዘቀዘ ሲሆን፣ በመንግሥት ደረጃ በዓሉ በድምቀት መከበር ቢቀርም እንኳ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ግንቦት 20 ላይ ዝግ በመሆን ቀጥለዋል።

ይሁን እንጂ ከ1984 ዓ.ም. ጀምሮ ሲከበር የቆየው ግንቦት 20 አሁን በሥራ ላይ ባለው የሕዝብ በዓላት እና የእረፍት ቀናት አዋጅ ላይ በሕዝብ በዓልነት አልተደነገገም። የኢህአዴግ መንግሥት በዓሉን ማክበር ከጀመረ አራት ዓመታት በኋላ በ1988 ዓ.ም. ይህንን አዋጅ ሲያሻሽልም ግንቦት 20ን በሕዝብ በዓላት ዝርዝር ውስጥ አላካተተውም።

የሕግ ባለሙያው አቶ አንዱዓለም፤ “እኔ እስከማውቀው ድረስ ግንቦት 20 ብሔራዊ በዓል የሆነበት ሕጋዊ መሠረት አለው ብዬ አላምንም” ሲሉ በዓሉ ሲከበር የነበረው ያለ ሕጋዊ እውቅና መሆኑን ያስረዳሉ። በአዋጅ የተደነገገ ጉዳይ የሚሻሻለውም ሆነ የሚሻረው በአዋጅ መሆኑን የሚያገልጹት አቶ አንዱዓለም፤ ግንቦት 20ን ግን የሚደግፍ አዋጅ ሳይኖር “በልምድ” ሲከበር መቆየቱን ጠቅሰዋል።

በተመሳሳይ መልኩ አሁን በሥራ ላይ ባለው አዋጅ ውስጥ በየዓመቱ መስከረም ሁለት ቀን በብሔራዊ በዓልነት እንዲከበር የተደነገገው የአብዮት መታሰቢያ በዓልም አህአዴግ ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ “በልምድ” መከበሩ እንዲቀር መደረጉን አንስተዋል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ታኅሣሥ 10/2016 ዓ.ም. ይህንን ረቂቅ አዋጅ ወደ ፓርላማ በመራበት ወቅት ቢቢሲ ያነጋገራቸው የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር የሕግ አገልግሎት ሥራ አስፈጻሚ አቶ በላቸው ድሪባ ስለ ግንቦት 20 ለቀረበላቸው ጥያቄ “[በብሔራዊ በዓልነት] ያካተትናቸው የኢትዮጵያን ሕዝብ ታሪክ ነው” የሚል ምላሽ ሰጥተው ነበር።

አቶ በላቸው፤ “[በረቂቅ አዋጁ ላይ] ይዘን የወጣነው ‘የሕዝብ ናቸው፣ ሰው ተቀብሏቸዋል’፤ እንደ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ፣ አገር፣ ዜጋ በጋራ የምንስማማባቸውን ነው” ሲሉ በሕዝብ በዓልነት ስለተቀመጡት በዓላት ገልጸዋል።

የሕግ ባለሙያው አቶ አንዱዓለም እንደሚያስረዱት ለፓርላማው በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ግንቦት 20 ሳይጠቀስ መቅረቱ በዓሉ ከዚህ በኋላ እንደማይከበር የሚያመለክት መሆኑን አስረድተዋል።

የሕግ ባለሙያው፤ “[በአዲሱ አዋጅ] ‘ኢትዮጵያ ውስጥ የሚከተሉት በዓላት ብሔራዊ በዓላት ሆነው ተደንግገዋል’ ተብሎ ከተዘረዘረ እና አንድ [ቀድሞ የነበረ] በዓል እዚህ ውስጥ ከሌለ፤ ከዚህ ቀደም በአዋጅ ውስጥ ቢኖር ራሱ በአመላካችነት (impliedly) ተሽሯል ብለን መውሰድ እንችላለን” ሲሉ ሀሳባቸውን አብራርተዋል።

አክለውም፤ “[ረቂቅ አዋጁ] ግንቦት 20 መሻሩን በግልጽ ባይጠቅስ እንኳ ዘሎታል። ስለዚህ ከአሁን ወዲህ ግንቦት 20 ብሔራዊ በዓል ነው ብለን መከራከር የምንችልበት አግባብ አለ ብዬ አላምንም” ብለዋል።

ከዚህም ባሻገር ረቂቁ፤ “ከዚህ አዋጅ ጋር የሚቃረን ማንኛውም አዋጅ፣ ደንብ፣ መመሪያ ወይም ልማዳዊ አሠራር በዚህ አዋጅ በተሸፈኑ ጉዳዮች ላይ ተፈፃሚነት አይኖረውም” በሚል ማስቀመጡ “በልምድ” ሲከበር የነበረው ግንቦት 20 እንደሚቀር አመላካች መሆኑን ገልጸዋል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ ፡-(bbc)