ቦይንግ ሰራሹ አውሮፕላን የአደጋ ጊዜ መውጫ በሩ በረራ ላይ የተገነጠለው ብሎኖች ጎድለውት ነው ተባለ

ከጥቂት ሳምንታት በፊት ቦይንግ 737 ማክስ 9 አውሮፕላን በረራ ላይ ሳለ የአደጋ ጊዜ መውጫ በሩ የተገነጠለው አራት ብሎኖች ጎድለውት ነው ተባለ።

ይህ የተገለጸው የአሜሪካ ብሔራዊ የትራንስፖርት ደኅንነት ቦርድ ክስተቱ ያጋጠመው አውሮፕላን ዙሪያ ያደረገውን የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት ባወጣበት ወቅት ነው።

ሪፖርቱ የአደጋ ጊዜ መውጫ በሩን አስረው መያዝ የነበረባቸው አራት ብሎኖች በቦታቸው አልነበሩም ብሏል።

ለመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርቱ ምላሹን የሰጠው አውሮፕላን አምራቹ ቦይንግ ለችግሩ ተጠያቂው እኔ ነኝ ብሏል።

የቦይንግ ፕሬዝዳንት ዴቭ ካልሁን “ከፋብሪካችን በሚወጣ አውሮፕላን ላይ ይህ አይነት ነገር መከሰት የለበትም። ለደንበኞቻችን እና ለተሳፋሪዎቻቸው የተሻለ ነገር መሠራት አለብን” ካሉ በኋላ አየር መንዶች በቦይንግ ላይ እምነት እንዲኖራቸው አጠቃላይ እቅድ አውጥተን እየተገበርን ነው ብለዋል።

ንብረትነቱ የአላስካ አየር መንገድ የሆነው 737 ማክስ 9 አውሮፕላን ለበረራ ከተነሳ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ የአደጋ ጊዜ መውጫ በሩ ከተገነጠለ በኋላ በአስቸኳይ ለማረፍ ተገዶ ነበር።

ክስተቱን ተከትሎ 737 ማክስ 9 አውሮፕላን በመላው ዓለም ከበረራ ታግዶ እንዲቆይ ተደርጓል።

ክስተቱ ያጋጠመው የአላስካ አየር መንገድ አውሮፕላን በኦሬጎን ግዛት ከፖርትላንድ ከተማ ተነስቶ ወደ ካሊፎርኒያ ሲበር ነበር። በአውሮፕላኑ ተሳፍረው የነበሩት 177 ተሳፋሪዎች እና ሠራተኞች ምንም ጉዳት ሳይደርስባቸው አውሮፕላኑ አርፏል።

737 ማክስ 9 አውሮፕላን ላይ ያጋጠመውን ክስተት የመረመረው የደኅንነት ቦርድ የተገነጠለው በር የተሰራው የቦይንግ አቅራቢ በሆነው ስፒሪት ኤየሮሲስተምስ መሆኑን አሳይቷል።

የመጀመሪያ ደረጃ የምርመራ ሪፖርቱ እንደሚለው ከሆነ ስፒሪት ኤየሮሲስተምስ በሩን የአውሮፕላኑ አካል ላይ ገጥሞ ቢያስረክብም ቦይንግ ደርሶ በምርት ሂደት ላይ ችግር ተገኝቶ የአደጋ ጊዜ መውጫ በሩ እንዲፈታ ተደርጎ ተመልሶ ሲገጠም አራት ብሎኖች ጎድለዋል።

ይህ ሪፖርት የቦይንግን ትልቅ ስህተት የሚያሳይ ነው ተብሏል። ከዚህም በላይ በተመሳሳይ ዝርያ ባለቸው ሌሎች አውሮፕላኖች ሊላላ የሚችል ብሎን መኖሩ መታወቁ የኩባንያው የጥራት ቁጥጥር ስልት ደካማ መሆንን አመላካች ሆኗል።

ይህ ቦይንግ ሰራሹ አውሮፕላን ባለፉት ዓመታት መነጋገሪያ ሆኖ ቆይቷል። ከአምስት ዓመት በፊት በኢትዮጵያ እና ኢንዶኔዢያ ባጋጠመ አደጋ ምክንያት ከበረራ ታግዶ የነበረው ይህ ማክስ 737 ዝርያ መሆኑ ይታወቃል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዝዝ ብቻ ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤ ለተጨማሪ መረጃ ድህረ ገጻችንን ይጎብኙ። https://ethio-amazon.com/
ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazonnnn

ምንጭ (ቢቢሲ)