በኢትዮጵያ በጎርፍ አደጋ አንድ ሚሊዮን የሚሆኑ ሠዎች ሊፈናቀሉ እንደሚችሉ የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ገለጸ……

ኢትዮጵያ ካሏት ሦስት ወቅቶች ውስጥ አንዱ የሆነውና አራት ወራትን የሚይዘው የበልግ ወቅት በደቡብ አጋማሽ ለሚገኙ የአገሪቱ አካባቢዎች ዋነኛ የዝናብ ወቅት ነው።

ከየካቲት እስከ ግንቦት ያሉትን ወራቶችን በሚሸፍነው የበልግ ወቅት ለሶማሌ፣ ጉጂ፣ ቦረና፣ ሲዳማ፣ ደቡብ ኢትዮጵያና ለደቡብ ምዕራብ የአገሪቱ ክፍሎች 55 በመቶ የዝናብ ስርጭታቸውን ያስገኛሉ።

የበልግ ወቅት ለምስራቅና ደቡብ ትግራይ፣ ለሰሜንና ደቡብ ወሎ ዞኖች፣ ለአማራና ኦሮሚያ ሰሜን ሸዋ ዞኖች፣ እንዲሁም አዲስ አበባን ጨምሮ ለመካከለኛው የአገሪቱ አካባቢ፣ ለምስራቅ አካባቢዎች (ሀረርና ድሬዳዋ) ሁለተኛ የዝናብ ወቅት ተደርጎ ይወሰዳል።

የኢትዮጵያ ሚትዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የ2016 ዓ.ም. የበልግ ወቅት በተለይም ዋነኛና ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑ አካባቢዎች ከመደበኛ በላይ የሆነ የዝናብ መጠንና ስርጭት እንደሚኖራቸው ትንበያ አውጥቷል።

ባለፉት ሳምንታት ዋና ከተማዋን አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በደረሱ የጎርፍ አደጋዎች የሠው ሕይወት እልፈትና ለንብረት ጉዳት ደርሷል። በአዲስ አበባ በደረሰው አደጋ አራት ሰዎች በጎርፍ ተወስደው ህይወታቸውን ማለፉን የአዲስ አበባ ከተማ የእሳት እና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ለቢቢሲ አረጋግጧል።

በሳምንቱ መገባደጃ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሀላባ ዞን በደረሰ የጎርፍ አደጋ አምስት ሠዎች ሕይወት ማለፉን የዞኑ አስተዳደር አስታውቋል።

ለጎርፍ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎች የትኞቹ ናቸው?

በኢትዮጵያ በክረምትና በበልግ ወቅቶች ከፍተኛ በሆነ የዝናብ መጠንና ስርጭት ምክንያት ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ ናቸው ተብለው ከተለዩ አካባቢዎች መካከል የአዋሽ ተፋሰስ፣ የሽምጥ ሸለቆ፣ የዋቢ ሸበሌ ተፋሰስ፣ ኦሞ-ጊቤ ተፋሰስ እንደሚጠቀሱ የሚቲዎሮሎጂ ትንበያ እና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ዘርፍ ምክትል ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር አሳምነው ተሾመ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“65 በሚደርሱ የአገራችን አካባቢዎች ላይ እስከ ዛሬው ከ30 እስከ 113 ሚሊ ሜትር ከባድ መጠን ያለው ዝናብ የተመዘገበባቸው [ናቸው]። . . . ተደጋጋሚነት ያለው የዝናብ መጠን በሚኖርበት ወቅት አፈሩ ውሃ የመሸከም አቅሙ ከእለት ወደ እለት እየቀነሰ የመሄድ አዝማሚያ ሊኖር ይችላል። ይህ ሁኔታም በቀላሉ ወደ ቅጽበታዊ ጎርፍ የመከሰት እድሉ ከፍተኛ [ነው]” ብለዋል።

የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (ኦቻ) አንድ ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን የሚጠጉ ሠዎች ለጎርፍ ተጋላጭ መሆናቸውን ይፋ አድርጓል።

በተለይ ደቡብ ኢትዮጵያ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ ሲዳማ፣ ኦሮሚያ (ደቡብ ኦሮሚያ)፣ ሶማሌ፣ አማራ፣ አፋር ክልሎችና ድሬዳዋና ሀረር (በከፊል) በጎርፍ ይጠቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በአገሪቱ ዘጠኝ የሚሆኑ ክልሎች ለጎርፍ ተጋላጭ ናቸው ተብለው ተለይተዋል። በእነዚህ ክልሎች በተለያዩ ወረዳዎች አንድ ሚሊዮን የሚሆኑ ሠዎች በጎርፍ አደጋ ሊፈናቀሉ ይችላሉ ተብሎ እንደተገመተ የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ለቢቢሲ ተናግሯል።

ትልቁን የስጋት ቀጣና የሚሸፍነው ሶማሌ ክልል ሲሆን፤ እንደ ኦቻ መረጃ ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ ሊሆኑ ይችላሉ ተብለው ከተገመቱ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሠዎች ውስጥ 773 ሽህ ሚሆኑት ይፈናቀላሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በኦሮሚያ በተለይም በጉጂ፣ ቦረና፣ አርሲና ባሌ አካባቢዎች 421 ሽህ የሚሆኑ ሠዎች ተጋላጭ ናቸው ተብለው የተለዩ ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ 104 ሽህ የሚሆኑ ሠዎች ሊፈናቀሉ እንደሚችሉ ይገመታል።

በደቡባዊ ክልሎችም 145 ሽህ ሠዎች ለጎርፍ ተጋላጭ ይሆናሉ ተብሎ ግመታ ወጥቷል።

ባለፉት ሳምንታት አዲስ አበባና ድሬዳዋና ጨምሮ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የጎርፍ አደጋ ተከስቶ የሠዎች ሕይወት ማለፉን የአካባቢዎቹ አስተዳደር አስታውቀዋል።

ይሁን እንጂ ኮሚሽኑ እስካሁን በደረሱ አደጋዎች የምን ያህል ሠዎች ሕይወት እንዳለፈ “የተጠናከረ” መረጃ የለኝም ብሏል።

የኮሚሽኑ የቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃና ኦፕሬሽን ማስተባበሪያ ስራ አስፈጻሚ ተወካይ የሆኑት ዶ/ር ፍራኦል በቀለ እስካሁን በደረሱ የጎርፍ “ክስተቶች” ሠዎችን ለማዳን አሊያም እንስሳትን ለመመለስ በሚደረግ ጥረት ውስጥ የሠዎች ሕይወት ማለፉን ገልጸው፤ የምን ያህል ሠዎች ሕይወት እንዳለፈ ግን አልገለጹም።

“ከአቅም በላይ የጎርፍ አደጋ ተከስቶ ሠውን ለሞት ዳርጓል የሚል የተጣራ መረጃ በእኛ በኩል የለም። . . . በጎርፍ ነው የተወሰዱት ወይም የሞቱት ለማለት ያስቸግራል” ብለዋል።

እስካሁን በተከሰቱ የጎርፍ አደጋዎች የተፈናቀሉ ሠዎች ምን ያህል ይሆናሉ ሲል ቢቢሲ የጠየቃቸው ዶ/ር ፍራኦል፤ በመንግሥት በኩል “በከፋ ደረጃ” የሚገለጽ ቁጥር የለም ሲሉ በአደጋው ሠዎች ለአንድ ቀን ብቻም ሊፈናቀሉ እንደሚችሉ አስረጂ ጠቅሰዋል።

በግንቦት ወር የተጠናከረ የዝናብ ስርጭት እንደሚኖር የሚጠበቅ ሲሆን ሠዎች ለጎርፍ አደጋ ጥንቃቄ እንዲያደርጉም ጥሪ ቀርቧል።

“ካለፉት ወራቶች ይልቅ ይህኛው [ግንቦት ወር] ትንሽ የከፋ እንደሚሆን ይጠበቃል። ይህንም ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት መከላከል ስራዎችን፤ የጥንቃቄ ስራዎችን ማሕበረሰቡ ሊወስድ ይገባል” ብለዋል።

የዘንድሮው የበልግ ዝናብ ለምን ጠነከረ?

በዘንድሮው የበልግ ወቅት ከመደበኛ በላይ የዝናብ ስርጭት እንደሚኖር ትንበያ መሰጠቱን ዶ/ር አሳምነው ተሾመ ተናግረዋል።

ዓለም አቀፍ የአየር ክስተቶችን መሰረት አድርጎ ትንበያ የሚሰጠው ኢንስቲትዩቱ፤ ኤልኒኖ የተባለው የአየር ክስተት (የምስራቅና የመካከለኛው ፓስፊክ ውቅያኖስ ከመደበኛ በላይ መሞቅ) ምክንያት በልግ ዋነኛና ሁለተኛ የዝናብ ምንጫቸው በሆኑ የአገሪቱ ክፍሎች ከመደበኛ በላይ የሆነ የዝናብ ስርጭት እንደገጠማቸው ገልጸዋል።

እንዲሁም ምዕራባዊና ሰሜናዊ የህንድ ውቅያኖስ ከመደበኛው ጋር የተቀራረበ የባህር ወለል ሙቀት የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ የሆኑ አካባቢዎች ከመደበኛ በላይ ሆነ የዝናብ መጠንና ስርጭት እንዲኖር አስተዋጽኦ እንደሚያደርግም ኃላፊው ጠቅሰዋል።

በአረብና ቀይ ባህር የተፈጠረው ተደጋጋሚ ዝቅተኛ የአየር ግፊት የበልግ ዝናብ እንዲጠናከር ማድረጉን ያነሱት ኃላፊው፤ 65 በሚደርሱ አካባቢዎች ላይ ከባድ የዝናብ መጠን የተመዘገበባቸው አካባቢዎች እንዳሉ ተናግረዋል። በዚህም በሆሳዕና፣ ባቲ፣ አዲስ አበባ፣ ሀላባ፣ ሞያሌና ጉጂ ቅጽበታዊ ጎርፍ መከሰቱን ዶ/ር አስማማው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ሚትዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት በግንቦት ወር ከቀደሙት ሦስት የበልግ ወራት በመጠንም ሆነ በስርጭት የተሻለ ዝናብ በበርካታ የአገሪቱ አካባቢዎች ሊኖር እንደሚችል ትንበያውን አስቀምጧል።

በዚህም በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ ከባድ ዝናብ አዘውትሮ የሚዘንብ ሲሆን በሰሜን ምስራቅ፤ ስምጥ ሸለቆ፤ ምስራቅ፣ ደቡብና ደቡብ ምስራቅ አከባቢዎች “ቅጽበታዊ ጎርፍ” ሊከሰት እንደሚችል ይጠበቃል ብሏል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ ( ቢቢሲ ዜና )