በአዲስ አበባ የተገደሉ ‘የፋኖ አባላት’ አስከሬን ይሰጠን ጥያቄ እስካሁን ምላሽ አለማግኘቱን ወላጆቻቸው ተናገሩ

በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ ሚሊኒዬም አዳራሽ አካባቢ ከፖሊስ ጋር በተደረገ የተኩስ ልውውጥ ከቀናትበፊት መገደላቸው የተነገረው የፋኖ አባላት ወላጆች የልጆቻቸው አስከሬን እንዲሰጣቸው ያቀረቡት ጥያቄ ምላሽ አለማግኘቱን ለቢቢሲ ተናገሩ።

ባለፈው ሳምንት አርብ ሚያዝያ 4/2016 ዓ.ም. የተገደሉት ናሁሰናይ አንዳርጌ እና አቤኔዘር ጋሻው ከሞቱ አራተኛ ቀናቸውን ቢያስቆጥሩም አስከሬናቸውን እስካሁን ማግኘት እንዳልቻሉ እናቶቻቸው ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ናሁሰናይ ከተገደለበት ማግስት ጀምሮ ቅዳሜ እና እሁድ አስከሬኑን ለማግኘት ሞክረው ያልተሳካላቸው እናቱ ወ/ሮ ሐረገወይን አዱኛ ያሉበትን ሁኔታ “ለእናት በጣም ከባድ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

ልጃቸው በተገደለ ማግስት ከጎንደር ወደ አዲስ አበባ የመጡት የአቤኔዘር ጋሻው አባተ እናት ወ/ሮ ኤልሳ ሰለሞን ደግሞ አስከሬን ለማግኘት ውጣ ውረድ እንደገጠማቸው ለቢቢሲ የገለጹት በለቅሶ ነው።

“ያሳዝናል፤ ህጻን ነው ደግሞ። አንድ ልጄን ምን ላድርግህ? ከባድ ነው” ብለዋል።

ሁለቱ ወጣቶች “የሽብር ተግባር ለመፈጸም በመንቀሳቀስ ላይ እያሉ በፀጥታ ኃይሉ በሰላም እጃቸውን እንዲሰጡ ተጠይቀው ፍቃደኛ ሳይሆኑ በፀጥታ አካላት ላይ ተኩስ ከፍተው በሁለት የፖሊስ አባላት ላይ ከባድ የአካል ጉዳት” እንዳደረሱ የፀጥታ እና ደኅንነት ግብረ ኃይል አርብ ዕለት ባወጣው መግለጫ አትቷል።

ሰኞ ሚያዝያ 7/2016 ዓ.ም. ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አምርተው የነበሩት የናሁሰናይ እናት ጉዳዩን የሚያየው የፌደራል ፖሊስ ነው የሚል ምላሽ ተሰጥቷቸዋል።

ፌደራል ፖሊስንም የልጃቸው አስከሬን እንዲሰጣቸው ጉዳዩን ጠቅሰው የማመልከቻ ደብዳቤ ያስገቡ ሲሆን “ይህ ነው የሚል ቁርጥ ያለ ምላሽ አልተሰጠንም” ይላሉ።

“ይሄንን ጉዳይ የአዲስ አበባ ፖሊስ ነበር መመለስ የነበረበት፤ ለምንስ እዚህ ድረስ መጣችሁ?” እንደተባሉ ገልጸዋል።

አክለውም “ዛሬ [ማክሰኞ] ደግሞ እንደገና ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ሄጄ የሚሉኝን እሰማለሁ” ሲሉም አስረድተዋል።

የልጃቸውን አስከሬን ለማግኘት ታችላይ እያሉ ያሉት እናት “ከባድ ነው ለእናት፤ በጣም ከባድ ከሚገባው በላይ። አስከሬን ነው የጠየቅኩት፤ ግድ ስለሆነ ምላሹን ለማግኘት ያው በተስፋ እየጠበቅኩ ነው። ምላሹንም ከመልካም ነገር ጋር እጠብቃለሁ” ሲሉ በሐዘን በተሰበረ ድምጽ ተናግረዋል።

የአቤኔዘር ጋሻው እናት ወ/ሮ ኤልሳ እንደ ናሁሰናይ እናት ተመሳሳይ ነገር ነው የገጠማቸው።

ሰኞ ዕለት ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አቅንተው ኃላፈውን እና ኮሚሽነሩን አግኝው ማናገር ባይችሉም

በዚያው የሚሠሩ ሠራተኞች ይህ ጉዳይ የሚመለከተው የፌደራል ፖሊስን ነው የሚል ምላሽ ተሰጥቷቸዋል።

የፌደራል ፖሊስ በትናንትናው ዕለት ምላሽ ያልሰጣቸው ሲሆን፣ ዛሬ ተመልሰው እንደሚሞክሩ ለቢቢሲ አስረድተዋል።

ወላጆቻቸው የልጆቻቸውን አስከሬን እስካሁን አለመቀበላቸውን በተመለከተ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ምክትል ኮማንደር ማርቆስ ታደሰን ቢቢሲ በስልክ የጠየቀ ሲሆን፣ እሳቸውም “መረጃው እንደሌላቸው እና ይሄ የሚመለከተው የፀጥታ እና ደኅንነት ግብረ ኃይል ወይም የፌደራል ፖሊስን እንደሆነ” ተናግረዋል።

ቢቢሲ የወላጆቹን ቅሬታ በማንሳት የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ጄላን አብዲንም ጠይቆ “እሳቸውም ይህ ጉዳይ የሚመለከተው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እንደሆነ” ገልጸዋል።

ልጃቸው ከተገደለ በኋላ ወደ አዲስ አበባ የመጡት ወ/ሮ ኤልሳ ጳውሎስ ሆስፒታል አምርተውም የልጃቸው ስም ዝርዝሩ ውስጥ እንዳለ ከተነገራቸውም በኋላ ከፖሊስ ትዕዛዝ ማምጣት እንዳለባቸው ተገልጾላቸዋል።

የአቤኔዘር አባት የልጃቸውን አስከሬን ለማምጣት ወደ አዲስ አበባ መጥተው እንደሆነ ቢቢሲ የጠየቃቸው እናት በምላሹም “ወንዶች ይታሰራሉ በሚል ፍራቻ አባትየው” እንዳልመጡና “እኔ እሻላለሁ ብለው እንደመጡ” አስረድተዋል።

ምክትል ኮማንደር ማርቆስ የፋኖ አባላት ናቸው ባሏቸው ናሁሰናይ አንድአርጌ ታረቀኝ፣ አቤኔዜር ጋሻው አባተ እና ሀብታሙ አንድአርጌ ተሰማ ላይ ፖሊስ ክትትል ሲያደርግ ቆይቶ ሚያዚያ 4/2016 ዓ.ም. በቁጥጥር ስር ለማዋል ሲሞክር በተሽከርካሪ ለማምለጥ መሞከራቸውን ለቢቢሲ መግለጻቸው ይታወሳል።

ተጠርጣሪዎቹ ዲዛዬር መኪና በመጠቀም በፖሊስ አባላት ላይ ተኩስ መክፈታቸው ተገልጿል።

በስፍራው በተተኮሰበት ጥይት አቤኔዘር ጋሻው ወዲያውኑ ሕይወቱ ሲያልፍ፣ ፖሊስ የፋኖ መሪ ነው ያለው ናሁሰናይ አንዳርጌ ታረቀኝ በተኩስ ልውውጡ ከቆሰለ በኋላ ወደ ህክምና ተወስዶ ሕይወቱ አልፏል ብሏል። ሌላኛው ግለሰብ ሃብታሙ አንዳርጌ በቁጥጥር ስር መዋሉ ተገልጿል።

ናሁሰናይ አንዳርጌ “የሽብር ጥቃት እንዲፈጽሙ የመለመላቸው ወጣቶች ሥልጠና እንዲወስዱ በማድረግ የፋይናንስ እና የሎጅስቲክስ ድጋፎችን ከአገር ውስጥ እና ከውጭ አገር ከሚገኙ ደጋፊዎቻቸው በማሰባሰብ ሁኔታዎችንም ሲያመቻች እንደነበር የግብረ ኃይሉ መግለጫ ጠቅሷል።

ግብረ ኃይሉ ጽንፈኛ ሲል የጠራው ቡድን አባላት “የሽብር ጥቃት ለማድረስ በአዲስ አበባ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች ህቡዕ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ” እንደነበር እና ክትትል እየተደረገባቸው ነበር ብሏል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ ፡-(World news)