በትግራይ ህፃናት እና እናቶች በከፋ የምግብ እጥረት እየተሰቃዩ ነው ተባለ

በትግራይ በከፍተኛ የምግብ እጥረት የተጠቁ ህፃናት እና እናቶች ቁጥር መጨመሩን የትግራይ ጤና ምርምር ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

የተቋሙ ዳይሬክተር ዶ/ር ሃየሎም ካህሳይ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ደም አፋሳሹ ጦርነት ቢያከትምም በክልሉ ያለው የእናቶች እና የህጻናት የምግብ እጥረት መሻሻል አላሳየም።

“ለረዥም ጊዜ ጦርነት ነበር። ከዚያም ድርቅ ተጨመረበት። የምግብ እጥረት ሊያጋጥም የሚችልበት ሁኔታ እንዳለ ይጠበቃል። በዚህ በጣም ተጋላጭ የሚሆኑትም ህጻናት፣ የሚያጠቡ እናቶች እና ነፍሰ ጡር ሴቶች ናቸው። ከጦርነቱ በኋላ የአመጋገብ ሁኔታው እንደሚሻሻል ጠብቀን ነበር። መረጃዎች ግን ብዙ ለውጥ እንዳልመጣ ነው የሚያሳዩት” ብለዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት በአንድ አካባቢ ያለው ከባድ እና መካከለኛ የተመጣጠነ የምግብ እጥረት በመለኪያው መሠረት ከ15 በመቶ በታች መሆን እንደሚገባው ቢደነግግም በትግራይ ግን ከ37 በመቶ በላይ መድረሱን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

በሰባት ወረዳዎች በተደረገ ቅኝት በተለይም ከ6 ወር እስከ 59 ወር ወይም 5 ዓመት የሆናቸውን ህጻናትን እንደተመለከቱ እና ከመካከላቸው 8.3 በመቶ የሚሆኑት ለአስገዳጅ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት የተጋለጡ መሆናቸውን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

“አማካይ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ደግሞ 29.3 በመቶ አካባቢ ነው። የሁለቱ ዓለም አቀፍ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ድምር የከፋ ሆኖ ወደ 37.6 ይደርሳል። በእናቶች ላይ የተደረጉ ጥናቶችም ተመሳሳይ ውጤት ያሳያሉ።”

በዓለም ጤና ድርጅት አሠራር መሠረት በአንድ አካባቢ ወይም ማኅበረሰብ ውስጥ ያለው አማካይ እና አስገዳጅ የምግብ እጥረት ከ15 በመቶ በላይ ከሆነ ‘ብላንኬት ከቨሬጅ’ ወይም ሁሉም ሰው ምግብ ያስፈልገዋል ማለት እንደሆነ የጠቀሱት ዶ/ር ሃየሎም፣ “ይህ እየታየ ያለው ከሰላም ስምምነቱ በኋላ ነው” ነው ብለዋል።

“የምግብ እጥረቱ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ነው”

በአንድ በጎ አድራጎት ድርጅት ውስጥ የሠሩ እና ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የህክምና ባለሙያ፣ በትግራይ በእናቶች እና ህጻናት ላይ እየታየ ያለውን የተመጣጠነ ምግብ እጥረት “አሳሳቢ” ሲሉ ገልጸውታል።

በተለያዩ አካባቢዎች በመንቀሳቀስ ጥናት እና እርዳታ እንዳደረጉ የሚገልጹት ባለሙያው በተለይም በክልሉ በማዕከላዊ ዞን ሁኔታው የከፋ መሆኑን ይናገራሉ።

“በተለይም ከአምስት ዓመት በታች ያሉ ህፃናት፣ ነፍሰ ጡር እናቶች እና አራሶች በአስከፊ የምግብ እና በመድኃኒት እጥረት ምክንያት ለህመም እና ለሞት እየተጋለጡ ነው” ብለዋል።

አደጋውን ለመከላከል የሚደረግ ጥረት በቂ እንዳልሆነ በማመልከትም፣ ለህጻናት በሚቀርበው አልሚ (ገንቢ) ምግብ ላይ እጥረት እና መቆራረጥ እንዳለ ገልጸዋል።

“አደጋውን ለመግታት እንቅስቃሴ ቢደረግም የሚመጣው አልሚ ምግብ (ፋፋ እና ፕላምፕኔት) በምግብ እጥረት ምክንያት እየተሰቃዩ ላሉት እናቶች እና ህጻናት በቂ አይደለም። ከ2 እስከ 3 ወራት አቅርቦቱ የሚቋረጥበት ሁኔታ አለ” ሲሉ ያስረዳሉ።

እንደ ባለሙያው ገለጻ ከሆነ በጎበኟቸው የትግራይ ዞኖች በሙሉ በሚባል መልኩ በተመጣጠነ ምግብ እጥረት የተጎዱ እናቶች እና ህጻናት ቁጥር እየጨመረ ነው።

ትግራይ ውስጥ በረሃብ የሚሞት ሰው ይኖር ይሆን?

ለሁለት ዓመታት በተካሄደው ጦርነት ምክንያት የመሠረተ ልማት ውድመት እና ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴ መስተጓጎል ባጋጠመበት ክልሉ ውስጥ የተከሰቱት ድርቅ፣ የአንበጣ ወረራ እና የሰብአዊ እርዳታ መቋረጥ ሳቢያ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በረሃብ መሞታቸውን የክልሉ ባለሥልጣናት እና የአገሪቱ እንባ ጠባቂ ተቋም መግለጻቸው ይታወቃል።

አንዳንድ የእርዳታ ድርጅቶች በትግራይ እና በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተውን ድርቅ በ1977 ዓ.ም. ተከስቶ ከነበረው ድርቅ እና ረሃብ ጋር በማነፃፀር ማስጠንቀቂያ ሲሰጡ ተደምጠዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ግን በትግራይ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ያጋጠመ ድርቅ እንጂ ረሃብ እና በረሃብ ምክንያት የሞተ ሰው የለም ሲል በመግለጫዎች አሳውቋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም ከቀናት በፊት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማብራሪያ በሰጡበት ጊዜ “በረሃብ ምክንያት የሚሞት ሰው የለም” ብለውም የተከሰተው ድርቅ የሰው ሕይወት እንዳይቀጥፍ መተባበር እንደሚገባ አሳስበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንዱ ክልል ተርቦ አንዱ በልቶ ሊያድር አይችልም ሲሉም ገልጸው ባለፉት ጥቂት ወራት በትግራይ ክልል 5 መቶ ሺህ ኩንታል እህል በመንግሥት እና በሌሎች አካላት ትብብር ወደ ክልሉ ማድረስ መቻሉን አስረድተዋል።

በዚህ ሳምንት ትግራይን የጎበኙት የዩናይትድ ኪንግደም የአፍሪካ ሚኒስትር ምንም አይነት እርምጃ ካልተወሰደ በአገሪቱ የረሃብ ምልክቶች እንደታዩ ገልጸዋል።

ትግራይ ውስጥ በረሃብ ምክንያት የሞቱ ሰዎች ካሉ የተጠየቁት የክልሉ ጤና ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ዶክተር ሃየሎም ካህሳይ የሰው ሕይወት መጥፋቱን “በሳይንሳዊ ጥናት አረጋግጠናል” ብለዋል።

“በዘጠኝ ወረዳዎች ውስጥ በሚገኙ ውስን መጠለያዎች ላይ ጥናት አድርገናል። የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመበት ከጥቅምት 24 እስከ ሐምሌ 24 ድረስ ያገኘነው አጠቃላይ የሟቾች ቁጥር 2,694 አካባቢ ነው። ይህ በዓለም ጤና ድርጅት መለኪያ ሲታይ ወደ 1,329 ወይም 68.3 በመቶው በረሃብ እና ከረሃብ ጋር በተያያዘ ያጋጠመ ሞት ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

የተመጣጠነ ምግብ እጥረት በልጆች ላይ የተለያዩ ችግሮች እንደሚያስከትል የጠቀሱት ዳይሬክተሩ በተለይ ጉዳቱ በነፍሰ ጡር፣ በሚያጠቡ እናቶች እና በጨቅላ ህጻናት ላይ የሚየደርሰው ጉዳት በቀጣይ ማኅበረሰባዊ እድገት ላይ ከባድ ጫና አለው ብለዋል።

“በተለይም የመጀመሪያዎቹ አንድ ሺህ ቀናት ወሳኝ ናቸው። ትግራይ ውስጥ በርካቶች በምግብ እጥረት ተጎጂ ሆነው አግኝተናል። ስለዚህ የሚወለዱት ህጻናት በአስተሳሰባቸው እና ትምህርትን የመቀበል አቅማቸው ላይ ውስንነት ይኖራል።”

መፍትሄው ምንድን ነው?

በትግራይ አስቸኳይ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ነዋሪዎች በሚቀርብ እርዳታ ላይ የተፈጸመው ስርቆት የእርዳታ ድርጅቶች ከወራት በፊት ሥርጭቱን እንዲያቆሙ ምክንያት ሆኗል። አንዳንድ ተቋማት ሥርጭት ቢጀምሩም በጣም ውስን እና ከነዋሪው ፍላጎት ጋር የማይመጣጠን ነው።

“እኔ አስደንጋጭ ዜና የምለው በየትኛውም አካባቢ ይሁን ‘በረሃብ ምክንያት ሰው ሞተ’ የሚል ዜና ነው” የሚሉት የትግራይ ጤና ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ዶ/ር ሃየሎም፣ ጊዜያዊ ሰብአዊ እርዳታ ከማቅረብ በተጨማሪ በዘላቂ ለውጥ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ መሠራት እንዳለበት ያምናሉ።

“በትግራይ ውስጥ ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ረሃብ ነው። ከክልል መንግሥት እስከ ፌዴራል መንግሥት ድረስ ኃላፊነት አለባቸው። ለጋሾችም የትግራይን ሕዝብ የመርዳት ጊዜው አሁን ነው። ዘላቂ መፍትሄዎችም እያስቀመጡ መሄድ ያስፈልጋል። መስኖን ማዘመን እና ሕብረተሰቡ ራሱ የሚያመርትበትን ሁኔታ ማመቻቸት ይገባል። የሥራ ዕድልም መፍጠር ያስፈልጋል” ብለዋል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዝዝ ብቻ ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤ ለተጨማሪ መረጃ ድህረ ገጻችንን ይጎብኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazonnnn

ምንጭ (ቢቢሲ)