በቅኝ ገዢዎች ከጋና ተሰርቀው ከ150 ዓመታት በኋላ ለዕይታ የበቁት ቅርሶች

ከጋናው የአሳንቲ ሥርወ መንግሥት በእንግሊዝ ቅኝ ገዢዎች የተመዘበሩ ቅርሶች ከ150 ዓመታት በኋላ ለዕይታ በቅተዋል።

የአሳንቲ መዲና በሆነው ኩማሲ በሚገኘው ማናህያ ቤተ መንግሥት ሙዝየም ውስጥ 32 ቅርሶች ለዕይታ ቀርበዋል።

“ዛሬ ቀኑ የአሳንቲ ነው። የጥቁር አፍሪካ ቀን ነው። የምንጋራው መንፈስ ተመልሷል” ሲሉ የአሳንቲ ንጉሥ ኦቱምፎ ኦሲ ቱቱ ተናግረዋል።

እነዚህ ቅርሶች ለሦስት ዓመታት ነው በውሰት ለጋና የተሰጡት። ሊራዘም ግን ይችላል።

የእንግሊዞቹ ሙዝየሞች ‘ዘ ቪክቶሪያ ኤንድ አልበርት ሙዝየም’ እና ‘ብሪትሽ ሙዝየም’ ከአሳንቴ ንጉሥ ጋር ባደረጉት ስምምነት ነው ውሰቱ የተከናወነው። በዚህ ስምምነት ውስጥ የጋና መንግሥት የለበትም።

አሳንቴኔ በመባል የሚጠሩት የአሳንቴ ንጉሥ የባህላዊ አስተዳደር ተምሳሌት ናቸው።ቅርሶቹ የንጉሡ አያት ቅድመ አያቶች መንፈስ አብሯቸው እንዳለ ይታመናል።

ይህ ሥርወ ግዛት አሁን የጋና አስተዳደር አካል ነው።የአሳንቲ አባል የሆነው ሄነሪ አማንክዊታ “ክብራችን ተመልሷል” ሲል ስሜቱን ይገልጻል።

ከሁለቱ ሙዝየሞች 17 እና 15 ቅርሶች በውሰት ተሰጥተዋል።

በማኅበረሰቡ ዘንድ የቅርሶቹ መመለስ ደስታን ፈጥሯል።ከእነዚህ ቅርሶች መካከል የተወሰኑት የተሰረቁት በአንግሎ-አሻንቲ ጦርነት በ19ኛው ክፍለ ዘመን ነው። ሌሎቹ ደግሞ እአአ በ1817 ለእንግሊዝ ዲፕሎማት የተሰጡ ናቸው።

የቪክቶሪያና አልበርት ሙዝየም ዳይሬክተር ከዶ/ር ትሪሳም ሁንት፣ “እነዚህ ቅርሶች በኛ ይዞታ ሥር የመጡበትን አስቀያሚ ታሪክ እንገነዘባለን። የኢምፔሪያሊዝምና ቅኝ ግዛት ጠባሳ አለባቸው” ብለዋል።

ከተመለሱት ቅርሶች መካከል ‘መፖከፖመሶ’ የተባለ ሰይፍ ይገኛበታል። በአሳንቲ ሕዝብ ትልቅ ዋጋ የሚሰጠው ነው።

የጎሳ መሪዎች በዓለ ሲመት ላይ ቃለ መሀላ የሚፈጸምበት ነው።

የነገሥታት ታሪክ ምሁር ኦሲ-ቦንሱ ሳፎ-ካታና ለቢቢሲ እንደገለጹት፣ እነዚህ ቅርሶች ከአሳንቲ ሲወሰዱ የሕዝቡም ልብ፣ ቀልብና ማንነት አብሮ ተሰርቋል።

የቅርሶቹ መመለስ አነጋጋሪና ከፍተኛ ዋጋ የሚሰጠውም ነው። በዩናይትድ ኪንግደም ሕግ መሠረት፣ ሁለቱ ሙዝየሞች ውዝግብ የሚነሳባቸው ቅርሶችን በዘላቂነት መመለስ አይችሉም።

ቅርሶችን በውሰት መስጠት ወደ ባለቤት አገራቸው የመመለስ ሂደት ተደርጎ ነው የሚወሰደው።

አንዳንድ አገራት ግን ‘ውሰት’ የሚል አገላለጽ ዩኬ የቅርሶቹ ባለቤት እንደሆነች ትርጓሜ የሚሰጥ ነው ብለው ይከራከራሉ።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ ( ቢቢሲ ዜና )