በመንግሥት እና በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መካከል ሦስተኛ ዙር ድርድር ሊኖር እንደሚችል ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ተናገሩ

የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ከዚህ ቀደም ከመንግሥት ጋር በነበረው ድርድር የተዘጋጀውን “የመጨረሻ ሰነድ” የሚቀበል ከሆነ ሦስተኛ ዙር ድርድር ሊኖር እንደሚችል የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ተናገሩ።

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ፤ በኦሮሚያ ክልል ከሚንቀሳቀሰው እና መንግሥት ‘ሸኔ’ ከሚለው ታጣቂ ቡድን ጋር የሚደረግ ሦስተኛ ድርድር “ወደ ሰላም ለመምጣት ወይም እስከ መጨረሻው ላለመነገጋር” የሚወሰንበት የመጨረሻ ንግግር ሊሆን እንደሚችልም አመልክተዋል።

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ፤ ለሁለተኛ ጊዜ የተደረገው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እና የፌደራል መንግስት ድርድር ያለ ስምምነት ከተጠናቀቀ ወዲህ በጉዳዩ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ አስተያየት የሰጡት ሰኞ ታኅሣሥ 1/2016 ዓ.ም. ለመንግስት ቅርበት ባለው ፋና ቴሌቪዥን በተላለፈ ቃለ መጠይቅ ላይ ነው።

የኢትዮጵያ መንግሥት እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ታንዛኒያ ዛንዚባር ውስጥ እንዲሁም በዚህ ዓመት ኅዳር ወር መጀመሪያ ላይ ያደረጓቸው ሁለት ዙር ንግግሮች ያለውጤት መጠናቀቁ ይታወሳል።

ኢታማዦር ሹሙ ለቴሌቪዥን ጣቢያው በሰጡት ቃለ መጠይቅ ላይ ካለፈው ጥቅምት ወር መጨረሻ እስከ ኅዳር 11 ድረስ በታንዛኒያ ዳሬ ሰላም የተደረገው ሁለተኛው ዙር ድርድር ላለመሳካቱ ምክንያት ያሏቸውን ጉዳዮች አብራርተዋል።

የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አዛዥ ኩምሳ ድሪባን እና ሌሎች የጦሩ አዛዦች ለመጀመሪያ ጊዜ ከፌደራል መንግሥት ከፍተኛ አመራሮች ጋር ፊት ለፊት የተገናኙበት ሁለተኛው ዙር ድርድር “በስምምነት ይቋጫል” የሚል ተስፋ በብዙዎች ዘንድ ፈጥሮ ነበር።

ድርድሩ ከተጀመረ ከቀናት በኋላ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እና የፍትህ ሚኒስትሩ ጌዴዎን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ንግግሩን መቀላቀላቸውም በጥሩ ምልክትነት ተወስዶ ነበር።

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑም ድርድሩ “በጥሩ ሁኔታ” እየተካሄደ እንደነበር የተናገሩ ሲሆን፣ በሁለቱ አካላት መካከል አለመስማማትን የፈጠሩ ጉዳዮች የተነሱት መጨረሻ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

“የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና አንድነትን መቀበል ላይ፣ የኢትዮጵያን አገረ መንግሥት፣ በምርጫ የመጣ ቅቡልነት ያለው መንግሥት መሆኑ ላይ መግባባት ተደረሰ። ከዚያ [ግን] በዝርዝሩ ነው እነዚህን መግባባቶች የሚሸረሽር ነገር የመጣው” ሲሉ መጀመሪያ ላይ ሁለቱ አካላት የተግባቡባቸውን ጉዳዮች ጠቅሰዋል። በዚህ ድርድር ላይ “አደራዳሪዎች እንኳ ያመኑበት የመጨረሻ ሰነድ” ተዘጋጅቶም እንደነበር አስታውሰዋል።

ኢታማዦር ሹሙ አለመግባባት አምጥተዋል ካሏቸው “ዝርዝር ጉዳዮች” መካከል በቀዳሚነት የጠቀሱት “ሥልጣን አካፍሉኝ” በሚል ቀርቧል ያሉትን ጥያቄ ነው። የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ይህንን ጥያቄ ያቀረበው የራሱን “ፕሮፖዛል” አዘጋጅቶ መሆኑን ያነሱት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ፤ “መሠረታዊ ልዩነት የፈጠረውን” ይህንን ጥያቄ መንግሥት እንዳልተቀበለው ተናግረዋል።

“መንግሥት ሥልጣን ላካፍል ቢልም ሥልጣን ማካፈል አይችልም። ሥልጣን የማካፈል መብት የለውም። ማድረግ የሚችለው ማሳተፍ ነው። ማሳተፍ ይችላል፤ ማካፈል ግን አይችልም። መጀመሪያውኑ ለምን ወደ ምርጫ ተሄደ?” ሲሉ የኢትዮጵያ መንግሥት በምርጫ ሥልጣን ላይ የተቀመጠ መሆኑ የታጣቂ ቡድኑ ጥያቄ ውድቅ እንዲሆን ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል።

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ፤ በሁለተኛነት የጠቀሱት ሁለቱን አካላት ያላግባባ ጉዳይ ትጥቅ መፍታትን የሚመለከት ነው።

ከመንግሥት ጋር ድርድር የሚቀመጥ አካል ጥያቄዎቹን ማንሳት ያለበት “ወደ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ለመመለስ፣ በሰላም ለመታገል፣ ፓርቲ አቋቁሞ ለመታገል፣ ለሕዝብ ምርጫ ለመቅረብ፣ የገጠር ትጥቅ ትግል ትቶ በሰላማዊ መንገድ ወደ ሕዝብ ለመመለስ“ ተስማምቶ መሆን እንዳለበት ገልጸዋል።

የታጣቂ ቡድኑ አባላትም ትጥቅ መፍታት፣ መበተን እና ወደ ሕብረተሰቡ መዋሃድ እንዳለባቸው የተናገሩት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ፤ በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አመራሮች ዘንድ ግን ይህንን ጉዳይ “ለመቀበል የመቸገር ነገር ተከስቷል” ሲሉ ወቅሰዋል።

“ይሄንን ካልተቀበልክ ድርድር ብሎ ነገር የለም። ይሄንን ያለቀመበል ችግር አለ። ስለዚህ [ድርድሩ] ጥሩ ሄዶ ሄዶ የቆመው በእነዚህ ሁለት ምክንያቶች ነው” ብለዋል።

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ፤ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አመራሮች ሁለቱን ነጥቦች “በተሳሳተ መንገድ እንዲወስዱ” በማድረግ ረገድ “ሌሎች ኃይሎች እጃቸው” እንዳለበት በቃለ መጠይቁ ላይ ተናግረዋል።

ኢታማዦር ሹሙ፤ “በዚህ ኃይል [ኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት] ላይ ታዝለው የሚሄዱ ኃይሎች አሉ። በዚህ ኃይል ተሸካሚነት የሚሄዱ ኃይሎች አሉ። አገር ውስጥም ከአገር ውጪም፤ ባዕዳንም፣ ዜጎችም። እነዚህ ኃይሎች፤ ይሄ ኃይል ነገሮችን በሰከነ መንገድ አይቶ ስምምነት እንዳይቀበል አድርገውታል” ሲሉ ለድርድሩ አለመሳካት በስም ያልጠቀሷቸውን ኃይሎች ተጠያቂ አድርገዋል።

አክለውም፤ “ችግር ውስጥ ያሉት እነሱ [ኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት] ናቸው፤ [በድርድሩ ላይ] ራሳቸው መወሰን ነበረባቸው። ሌላው ኃይል ጣልቃ ስለገባ በዓለም ልምድ ታይቶ የማይታወቅ ቅድመ ሁኔታ በማቅረብ መንግሥትን አስቸግረዋል” ብለዋል።

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ይህንን ቢሉም ከድርድሩ መጠናቀቅ በኋላ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ባወጣው መግለጫ ለድርድሩ አለመሳካት ተጠያቂ ያደረገው መንግሥትን ነበር።

እንደ ታጣቂ ቡድኑ ገለጻ በድርድሩ ከስምምነት ላይ መድረስ ያልተቻለው የኢትዮጵያ መንግሥት “የአገሪቱን ደኅንነት እና ፖለቲካን ፈተና ውስጥ ለከተቱ መሠረታዊ ችግሮች መፍትሄ ለመስጠት ፍላጎት ባለማሳየቱ” ነው ብሎ ነበር።

ከድርድሩ መጠናቀቅ በኋላ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትም ሆነ መንግሥት በተናጠል ባወጧቸው መግለጫዎች ላይ ሦስተኛ ዙር ድርድር ማድረግን በሚመለከት የተጠቀሰ ነገር አልነበረም።

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ግን ሰኞ ዕለት በቀረበው ቃለ መጠይቅ ላይ ሦስተኛ ዙር ድርድር ሊደረግ ይችላል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።

“ሦስተኛ ዕድል ይኖራል ወይ? የሚለው ሊኖር ይችላል። ምናልባት ሰከን ብለው አስበው። የመጨረሻ ሰነድ እኮ ተዘጋጅቷል፤ እነዚህ አደራዳሪዎች እንኳ የሚያምኑበት። እሱን ወደ መቀበል ደረጃ ከተደረሰ ሦስተኛ ዙር ውይይትም ሊኖር ይችላል” ሲሉ መንግሥት በሦስተኛውም ዙር ድርድር ከዚህ ቀደም የተዘጋጀው ሰነድ ላይ እንደሚመሠረት ጠቁመዋል።

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ፤ በመንግሥት እና በታጣቂ ቡድኑ መካከል ሊደረግ የሚችለው ቀጣይ ድርድር እንደ ሁለተኛው ዙር ድርድር “ሰፊ ውይይት” የማደረግበት ሊሆን እንደሚችልም ገልጸዋል።

“እስካሁን የተደከመበት ውይይት እና ሰነድ አለ። እሱን መቀበል ላይ ከተደረሰ ሦስተኛ [ዙር ድርድር] ሊኖር ይችላል። ሦስተኛው ውይይትም የመጨረሻ ይሆናል ብዬ እገምታለሁ። ወደ ሰላም ለመምጣት ወይም እስከ መጨረሻው ላለመነገጋር የመጨረሻ ሊሆን ይችላል” ሲሉ ቀጣዩ ድርድር የሁለቱን አካላት ወደፊት ግንኙት ለመበየን ወሳኝ መሆኑነ በአጽንኦት ተናግረዋል።

ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር ተነጥሎ በበርካታ የኦሮሚያ አካባቢዎች የትጥቅ እንቅስቃሴ እያደረገ የሚገኘው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ከሁለት ዓመት በፊት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብር ቡድንነት መፈረጁ ይታወቃል።

የታጣቂ ቡድኑ እንቅስቃሴ በተለይ በምዕራባዊው የአገሪቱ ክፍል ውስጥ የጎላ ሲሆን፣ ከመንግሥት ኃይሎች ጋር በሚካሄዱ ግጭቶች እና በሚፈጸሙ ጥቃቶች የአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ላላፉት አምስት ዓመታት ከባድ የሕይወት እና የንብረት ጉዳት መድረሱ ሲዘገብ ቆይቷል። ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ነዋሪዎችም ግጭቶች እና ጥቃቶችን በመሸሽ ከቀያቸው ተፈናቅለዋል።

ምንጭ ( ቢቢሲ ዜና)