በልጅነታቸው ተሽጠው በቲክቶክ የተገናኙት መንታ እህትማማቾች

አሚ እና አኖ መንታ ናቸው። እንደተወለዱ ከእናታቸው እቅፍ ተወስደው በተለያየ ቤተሰብ አደጉ። ከዓመታት በኋላ በአጋጣሚ በቲክቶክ ቪድዮ ተገናኝተዋል።

የተወለዱት ጆርጂያ ነው። በሺዎች የሚቆጠሩ ልጆች የሚሰረቁበት አገር ነው። አሚ እና አኖም ከእነዚህ መካከል ናቸው።

ኤሚ እና አኖ ሆቴል ውስጥ ሆነው ይጠባበቃሉ። “ጨንቆኛል። ምን እንደገጠመን መልስ ማግኘት አለብኝ” ትላለች።

አኖ ደግሞ ሶፋ ላይ ሆና ቲክቶክ እያየች ነው። “የሸጠችን ሴት ይቺ መሆን አለባት” ትላለች። ወላጅ እናታቸውን ለመጀመሪያ ጊዜ ሊያዩ እየጠበቁ ነው።

ከጆርጂያ ጀርመን ተጉዘው ነው እዚህ የደረሱት። በሕይወታቸው ያላወቁትን ነገር ለማወቅ ብዙ ደክመዋል። ወላጅ እናታቸውን ያገኛሉ። ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

ለሁለት ዓመት ይህን ቅጽበት ጠብቀዋል። እውነታን ማወቅ ይሻሉ። ታሪካቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ልጆችም ነው። ልጆች በጆርጂያ ከሆስፒታል ተሰርቀው ይሸጣሉ። ክስተቱ ለአሥርት ዓመታት የቆየ ነው። እስካሁን ተጠየቂ የሆነ የለም። ምርመራ ግን ተደርጓል።

አኖ በ12 ዓመቷ የክርስትና እናቷ ጋር ሳለች ቲቪ እያየች ነበር። ‘ጆርጂያስ ጋት ታለንት’ የተባለ የተሰጥኦ ውድድር ነው። በጣም ትወደዋለች። እሷን የምትመስል ልጅ ስትደንስ አየች። አኖ እየደነሰች የመሰላቸው ሰዎች ‘ለምን አኖ ስሟን አሚ ብላ በቲቪ ስትደንስ ታየች’ ሲሉ ጠየቁ። እውነታው ግን አሚ እና አኖ መንትዮች መሆናቸው ነው።

እናቷ ግን ሁሉም ሰው ቁርጥ እሱን የሚመስል ሰው አያጣም ብላ ዝም አለች። ከሰባት ዓመት በኋላ አሚ ቲክቶክ ላይ ቅንድቧን ስትቀነደብ ቪድዮ ለጠፈች።

 አኖ በጓደኛዋ ይህ ቪድዮ ሲላክላት ‘እኔን የምትመስል ሴት’ አለችና ተገረመች። ከዚያ ግን አሚን የሚያውቅ ሰው ማፈላለግ ጀመረች። አሚ ከዓመታት በፊት ያየቻች ሴት አኖ እንደሆነች ለማወቅ ጊዜ አልወሰደባትም።

በዩኒቨርስቲ ዋትስአፕ ላይ ተገናኙ። “ለዓመታት ስፈልግሽ ነበር” ብላ አሚ ጻፈች። አኖም “እኔም” ስትል መልስ ሰጠች። በጣም እንደሚመሳሰሉ አወቁ። የተወለዱት ክትሽኪ ሆስፒታል ነው። ልደታቸው ግን የሁለት ሳምንት ልዩነት አለው።

እህትማማቾች አንሆንም ብለው አሰቡ። የተወለዱበት ሆስፒታል ሥራ አቁሟል። የሚወዱት ሙዚቃ ተመሳሳይ ነው። ሁለቱም ዳንስ ይወዳሉ። በጣም እንደሚመሳሰሉ ሲያውቁ የበለጠ ተገረሙ።

በአካል የተገናኙት በተዋወቁ በሁለት ሳምንት ነበር። “መስታወት የማየት ያህል ነው። አንድ ዓይነት መልክ። አንድ ዓይነት ድምጽ” ትላለች አሚ። ያኔ ነው መንታ እንደሆኑ የጠረጠሩት።

“ሰው ማቀፍ ባልወድም እሷን ሳያት አቀፍኳት” ትላለች አኖ። ያሳደጓቸውን ቤተሰቦች ሲጠይቁ ሁለቱም የማደጎ ልጆች መሆናቸውን አወቁ።

እአአ ከ2002 ጀምሮ ተነጣጥለው አድገዋል። አሚ እውነታውን ስታውቅ ተናዳለች። ሕይወቷ የውሸት እንደነበር ተሰማት። “የማይመስል ቢሆን እውነተኛ ታሪክ ነው” ትላለች እንባ እየተናነቃት።

አኖ ቤተሰቦቿ እውነታነው ስለደበቋት ተቆጥታለች። መንትዮቹ በሳምታት ልዩነት እንደተወለዱ በማስመሰል የተሠራው የልደት ሰርተፍኬታቸው በምሥጢር የተያዘ ነበር። ግን በጋራ ደረሱበት።

የአሚ አሳዳጊ እናት ልጅ መውለድ ስለማይቸሉ ነው በማደጎ ያሳደጓት። አኖም እንደዚያው። መንታ እንደሆኑ ግን ያወቀ አልነበረም። ልጆቹን ለማግኘት ከፍተኛ ገንዘብ አውጥተዋል። ሕገ ወጥ እንደሆነ ግን አላወቁም።

ጆርጂያ ቀውስ ውስጥ ስትገባ ሆስፒታል ውስጥ የሚሠሩ ሰዎች ልጆችን መሸጥ ጀመሩ። መንትዮቹ የተሸጡት በእናታቸው መስሏቸው ነበር። እናትየዋ ግን ልጆቿ እንደሞቱ ነበር የተነገራት። “እንዴት ትከዳናለች?” ስትል አሚ በወላጅ እናታቸው አዝና ነበር። ወላጅ እናት ጥርጣሬ ቢገባትም ልጆቹ እንደሞቱ ተነግሯታል።

በጆርጂያ የተሰረቁ ልጆችን ከወላጆቻቸው የሚያገናኝ የፌስቡክ ገጽ ላይ አንድ ሴት አገኙ። በዘረ መል ምርመራ እህታቸው እንደሆነች ተረጋገጠ።

ስሟ አዚያ ነው። የምትኖረው ጀርመን ነው። እህታቸው እንደሆነች ከተረጋገጠ በኋላ ወላጅ እናታቸውን አገኙ።

አኖ እናታቸው እንደሸጠቻቸው በማመን ለማግኘት አልፈለገችም ነበር። አሚ ግን አበረታታቻት።

በፌስቡክ ገጹ ላይ ልጆቻቸው እንደሞቱ የተነገራቸው ግን ልጆቻቸው እንዳሉ የሚያምኑ ወላጆች መልዕክት ይለዋወጡ ነበር። ልጆቻቸውን ይፈልጉም ነበር።

የማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ታሙና ሙሲርዲዝ በተባለች ጋዜጠኛ ነው የተቋቋመው። ጋዜጠኛዋ በማደጎ እንዳደገች ካወቀች በኋላ ነው የጀመረችው። ብዙ ቤተሰቦችን አገናኝታለች።

ወንጀለኛ ቡድኖች ልጆችን በመስረቅ እጃቸው እንዳለበት ታምናለች። በዚህ ውስጥ ታክሲ ነጂዎች እና የመንግሥት ባለሥልጣናት ሳይቀሩ እጃቸው ይሳተፉበታል ብላለች።

በግምት ወደ 100 ሺህ ልጆች መሰረቃቸውንም ትገልጻለች። ልጆቻቸው እንደሞቱ የተነገራቸው እናቶች የልጆቻቸውን አስክሬን ለማየት ቢጠይቁም እንደተቀበሩ ይነገራቸዋል።

ሌሎች እናቶች ደግሞ ልጆቻቸው ያልሆኑ ነገር ግን የሞቱ ሕጻናት አስክሬን እንዲያዩ ይደረጋል። ልጆቹ ወደ አሜሪካ፣ ካናዳ፣ ቆጵሮስ፣ ሩሲያ እና ዩክሬን ተሸጠው ይወሰዳሉ። በጉዲፈቻ ያድጋሉ።

በ2006 (እአአ) የጆርጂያ መንግሥት የጉዲፈቻ ሕጉን ለውጧል። ሕገ ወጥ የልጆች ዝውውር እንዲቀንስ ለማድረግ በማሰብ ሕጎች ጠብቀዋል።

አንድ መንታ ልጆቿ እንደሞቱ የተነገራት እናት ነገሩን አምኖ ለመቀበል ቸግሯት እንደነበር ትናገራለች። ግን የልጆቿን አስክሬን ማየት እጅግ ከባድ ነው በሚል ነገሩ እንዲዳፈን ተደረገ።ልጆቹ ተቀብረዋል ተብሎ ጥቁር የአስክሬን ላስቲክ አሳይተዋት ነበር።

ከ44 ዓመት በኋላ ግን የእናትየዋ ሌላ ልጅ ኒኖ ወንድሞቿ እንዳልሞቱ አመነች። ተቀብረውበታል የተባለው ቦታ ተቆፈረ።

“ልክ ላስቲኩን ስንከፍተው አንድም አጥንት የለም። ለማልቀስም ለመሳቅም ግራ ተጋባን” ትላት ኒኖ።

አሚ እና አኖ ወላጅ እናታቸውን አግኝተዋታል። ይጠብቋት የነበረው ሆቴል ውስጥ ሆነው ተጨንቀው ነበር።

ልክ በሩ ሲከፈት አሚ እና አኖ በዝግታ ተመለከቱ። ማንም ለደቂቃዎች ቃል አላወጣም። ዝምታው ወደ ለቅሶ ተለወጠ።

እናትየዋ ልጆቹን እንደወለደች ታማ ኮማ ውስጥ ገብታ እንደነበር ነገረቻቸው። ልጆቿም እንደሞቱ ተነገራት። ከዚያ በኋላ ከእናታቸው ጋር ያላቸው ግንኙነት ቀጠለ።

ከሁለት ዓመት በፊት የጆርጂያ መንግሥት የልጆች ሕገ ወጥ ዝውውር ምርመራ ከፍቷል። ከ40 በላይ ሰዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት በተለያዩ ዓመታት በተደረገ ምርመራ የማዋለጃ ክፍል ኃላፊን ጨምሮ እጃቸው አለበት የተባሉ በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ተደርጓል።

ወላጆች እና ልጆችን በፌስቡክ ለማገናኘት የምትሠራው ጋዜጠኛ ሊያ ሙካሽቪራ ከተባለች ጠበቃ ጋር መሥራት ጀምራለች። ወደ ፍርድ ቤት ጉድዩ እንዲሄድም ይሠራሉ።

አኖ “በሕይወቴ እንዳች የጎደለ ነገር እንዳለ ይሰማኝ ነበር” ስትል ነው ከእህቷ እና ከእናቷ ተለያይቶ ለዓመታት መኖርን የምትገልጸው። አሚ ደግሞ “ያ የባዶነት ስሜት አኖን ሳገኝ ጠፋ” ትላለች።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዝዝ ብቻ ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤ ለተጨማሪ መረጃ ድህረ ገጻችንን ይጎብኙ። https://ethio-amazon.com/
ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ ( ቢቢሲ ዜና )