ቀይ ባሕርን ያወኩት ሁቲዎች ከባሕር በታች የተዘረጋ የኢንተርኔት መስመርን እንዳይቆርጡ ተሰግቷል

በቀል ዓይነቱ ብዙ ነው።

የየመን ሁቲዎች በአሜሪካ እየተመሩ የአየር ጥቃት የሚያደርሱባቸው ምዕራባውያንን ለመበቀል ወደኋላ እንደማይሉ አሳይተዋል።

አሜሪካ እና አጋሮቿ ሁቲዎች ሚሳዔል እና ድሮን ለመተኮስ የሚጠቀሙባቸውን ጣቢያዎች ደብድበዋል።

ሁቲዎች በጋዛ ያሉ ፍልስጤማውያንን ለመደገፍ ነው ብለው በቀይ ባሕር እና በኤደን ባሕረ ሰላጤ የሚመላለሱ መርከቦችን ዒላማ አድርገዋል።

አሁን ሁኔታዎች ተጋግለዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ዕውቅና የሚሰጠው ኤደን የሚገኘው የየመን መንግሥት ሁቲዎች ክፉ እያሰቡ፤ እስያ እና አውሮፓን የሚያገናኘውን የበይነ መረብ ገመድ ሊበጥሱት አቅደዋል ይላል።

ይህ የኢንተርኔት ገመድ ከቀይ ባሕር ስር በባሕሩ ወለል ላይ የተዘረጋ ነው።

የሁቲ አማፂያን አብዛኛውን የየመን ክፍል የተቆጣጠሩት በአውሮፓውያኑ 2014 ነው።

ይህ ማስጠንቀቂያ የመጣው ከሁቲዎች ጋር ግንኙነት አለው የሚባል አንድ የቴሌግራም ቻናል ቀይ ባሕር ውስጥ የተዘረጉ ገመዶችን የሚያሳይ ካርታ ከለጠፈ በኋላ ነው።

ሁቲዎች እኒህን ገመዶች ይበጥሱ ይሆን? ማድረግ ቢፈልጉ የሚከለክላቸው የለም።

አማፂያኑ እንደሚሉት በባሕር ውስጥ የተዘረጉትን ገመዶች የሚያሳይ ካርታ በቀላሉ አግኝተዋል፤ ገመዶቹ ደግሞ በባብ አል-ማንዳብ ሰርጥ በኩል ነው የሚያልፉት።

ነገር ግን ይህ 17 በመቶ የሚሆነውን የዓለም ኢንተርኔት መስመርን የሚያገናኙ ፋይበር ገመዶች መቶ ሜትሮች ወደ ታች ዘልቀው የባሕር ጠለል ላይ ነው የሚገኙት።

ይህ ማለት ቀዛፊዎች ሊደርሱባቸው አይችሉም ማለት ነው።

የዩናይትድ ስቴትስ እና የሩሲያ የባሕር ኃይሎች ግን ወደ ታች ዘልቀው ይህን ገመድ የመቁረጥ አቅም እንዳላቸው ይነገራል።

ይህን የሚያደርጉት የውቅያኖስ ወለልን መዳበስ የሚችል ሰርጓጅ ጀልባ ትልቅ መቀስ አዝሎ እንዲገባ በማድረግ ነው።

ሁቲዎች ይህንን ገመድ በቀላሉ መቁረጥ የሚችል አቅም የላቸውም።

የቀድሞው የብሪታኒያ ሮያል ባሕር ኃይል ሰርጓጅ መርከብ አዛዥ የሆኑት ሪር አድሚራል ጆፐን ጎወር “እንዲሁ ለማስፈራራት ካልሆነ በቀር አይችሉትም” ይላሉ።

“አቅም ያለው አጋር ያስፈልጋቸዋል። የሰርጓጅ መርከብ አቅም ያለውን ገመዶቹ የት እንዳሉ የሚያውቅ አጋር።”

ሁቲዎች አጋር አላቸው – ኢራን። ሁቲዎች የሚሳዔል እና የድሮን አቅርቦት የሚያገኙት ከኢራን አብዮታዊ ዘብ እና ከሊባኖሱ ሔዝቦላህ ነው።

እነዚህ የጦር መሣሪያዎች ላለፉት ስምንት ዓመታት ሳዑዲ አረቢያ እና ዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ ላይ ሲተኩሱ ከርመዋል። አሁን ደግሞ በእስራኤል፣ በአሜሪካ፣ በብሪታኒያ ጦር መርከቦች ላይ ጥቃት እያደረሱ ነው።

ከእስራኤል አሊያም ከአሜሪካ ወይ ደግሞ ከዩናይትድ ኪንግደም (የኬ) ጋር ግንኙነት አለው ያሉትን መርከብ ከማጥቃት ወደኋላ አይሉም።

ኢራን የየመን ሁቲ አማፂያን ከባሕር በታች ያሉ ገመዶችን እንዲበጥሱ ልታግዝ ትችላለች?

“ኢራን ይህ አቅም አላት የሚያስብል ነገር እስካሁን አላየሁም። ሰርጓጅ መርከባቸው ይህ አቅም በፍፁም የለውም” የሚሉት ደግሞ የቀድሞው የዩኬ ባሕር አባል የነበሩት ቶም ሻርፕ ናቸው።

እሳቸውም እንደ ቀድሞ አጋራቸው ጎወር “እንዲሁ ለማስፈራራት ነው” እንጂ ሁቲዎች ይህን ማድረግ አይችሉም ይላሉ።

አሜሪካም ሆነች ኢራን ወደለየለት ጦርነት መግባት አይሹም። ይህንን ደጋግመው አረጋግጠዋል።

አሜሪካ እና ኢራን በመካከለኛው ምሥራቅ በአጋሮቻቸው አማካይነት የሚያደርጉት ጦርነት አንዳች ዓይነት መከባበር ያለበት ነው።

አሜሪካ በኢራቅ እና በሶሪያ የሚገኙ በኢራን የሚደገፉ ታጣቂዎችን ስትመታ ከቀናት በፊት ማስጠንቀቂያ ሰጥታ ነው። ይህ ደግሞ ቁልፍ የሚባሉ ኢራናውያን ከሥፍራው እንዲርቁ ጊዜ ይሰጣል።

ዓለም አቀፍ ግንኙነት የሚያሳልጡ ገመዶችን መበጠስ ማለት አራን የመልሶ ማጥቃት እርምጃ እንዲወሰድባት ዕድል መስጠት ማለት ነው።

“አራን መሠረት ልማቱን ከማውደም ይልቅ የሳይበር ጥቃት ማድረስን ትመርጣለች” የሚሉት ከ2015-17 (እአአ) በየመን የዩኬ አምባሳደር የነበሩት ኤድመን ፊተን-ብራውን ናቸው።

ሁቲዎች በቅርቡ በቴሌግራም ገፃቸው የለጠፉት ማስፈራሪያን ተግባራዊ ለማድረግ ይከብዳቸዋል።

ይህ የሚሆነው ገመዱን መበጠስ ቀላል ስላልሆነ እና ለኢራን ደግሞ አደጋ ስለሆነ ነው። ቀይ ባሕርን አቋርጠው በሚሄዱ መርከቦች ላይ የኢራን እጅ አለበት ሲሉ ምዕራባውያን ወቀሳ ያሰማሉ።

ሁቲዎች ግን ከዚህ ቀደም አያደርጉትም የተባለ ተግባር ሲፈፅሙ አይተናል። በ2022 የሳዑዲ ነዳጅ ማከማቻ ላይ የፈፀሙት ጥቃትን ልብ ይሏል።

ለስምንት ዓመታት ያክል በሳዑዲ የሚመራው ኃይል ያደረሰባቸውን ጥቃት ተቋቁመው ሥልጣን ላይ መቆየት ችለዋል።

ዛሬም ቢሆን አሜሪካ እና አጋሮቿ በተደጋጋሚ የሚሳዔል እና የድሮን ጣቢያዎቻቸውን ቢደበድቡም ሁቲዎች ወደኋላ እንደማይሉ ግልጽ አድርገዋል።

በተለይ ከእነሱ ቁጥጥር ውጪ በሆኑ ሥፍራዎች በሚኖሩ የመናውያን ዘንድ የሚጠሉት እና የሚፈሩት ሁቲዎች በጥንቃቄ ሊያዙ የሚገባቸው ኃይል ሆነዋል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዝዝ ብቻ ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤ ለተጨማሪ መረጃ ድህረ ገጻችንን ይጎብኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazonnnn

ምንጭ (ቢቢሲ)