ሱዳናውያን ስደተኞችን ያሳፈረች ጀልባ ሰጥማ ቢያንስ አስራ ሦስት ሰዎች ሞቱ

ሱዳናውያን ስደተኞችን ያሳፈረች ጀልባ በቱኒዚያ ባህር ዳርቻ ሰጥማ ቢያንስ 13ቱ ሲሞቱ ሌሎች 27 ሰዎች መጥፋታቸውን የቱኒዚያ ባለሥልጣን ተናገሩ።

በጀልባዋ ላይ ተሳፍረው ከነበሩት ከ40 በላይ ስደተኞች በሕይወት የተገኙት ሁለት ሰዎች ብቻ ሲሆኑ የጠፉት እየተፈለጉ መሆኑን ባለሥልጣኑ ገልጸዋል።

አደጋው የደረሰው ጀልባዋ ከስፋክስ ከተማ አቅራቢያ ከምትገኝ ጀቢኒያና ከተባለች አነስተኛ መንደር ተነስታ እየተጓዘች ሳለ ነበር።

በቱኒዚያ የሞናስቲር ከተማ የፍትሕ ቢሮ ቃል አቀባይ ፋሪድ ቢን ጂሃ የአደጋው ምክንያት እየተጣራ መሆኑን ተናግረዋል።

ኤኤፍፒ የዜና ወኪል ቃል አቀባዩን ጠቅሶ እንደዘገበው ስደተኞቹ በሕገ ወጥ መንገድ ወደ አውሮፓ ለመግባት በሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች አሊያም በወንጀለኛ ቡድኖች ብዝበዛ የደረሰባቸው ሊሆኑ ይችላሉ።

ይህ ስደተኞች ከአፍሪካ ተነስተው አውሮፓ ለመግባት የሜዴትራኒያን ባህርን ለማቋረጥ ሲሞክሩ የተከሰተ የቅርብ ጊዜ አደጋ ነው።

ሱዳን ከአስር ወራት በፊት የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ የገባች ሲሆን ይህም ቢያንስ ዘጠኝ ሚሊዮን ሰዎች አካባቢያቸውን ጥለው እንዲሰደዱ አስገድዷል።

ከእነዚህ መካከል አብዛኛዎቹ በአገሪቷ ውስጥ አንጻራዊ ሰላም ባለባቸው አካባቢዎች እንዲሁም በጎረቤት አገራት ተጠልለው ይገኛሉ።

ባለፈው ሚያዚያ ወር በሱዳን ጦር እና በተቀናቃኙ ልዩ ኃይሎች መካከል ግጭት ከተከሰተ በኋላ የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥትን ጨምሮ የተወሰኑ የውጭ መንግሥታት በእርስ በእርሱ ጦርነት አጣብቂኝ ውስጥ ገብተው የነበሩ ዜጎቻቸውን አስወጥተዋል።

እንደ ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት አይኦኤም ከሆነ እንደ አውሮፓውያኑ 2023 ማዕከላዊ የሜዲትራኒያን ባህርን ለማቋረጥ ሲሞክሩ ከ2 ሺህ 270 በላይ ስደተኖች ሞተዋል። ይህም ከቀደመው ዓመት ጋር ሲነጻጸር 60 በመቶ ጨምሯል።

ባለፈው ዓመት የአውሮፓ ኅብረት ሕገ ወጥ ስደትን ለመከላከል ከቱኒዚያ ጋር ስምምነት ተፈራርመው ነበር።

ስምምነቱ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለማስቆም፣ ድንበሮችን ለማጠናከር እና ስደተኞችን ለመመለስ የሚውል የ118 ሚሊዮን ዶላር ገንዘብን ያካትታል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዝዝ ብቻ ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤ ለተጨማሪ መረጃ ድህረ ገጻችንን ይጎብኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazonnnn

ምንጭ (ቢቢሲ)