መነኩሴ ግድያውን ፈጽሟል ከተባለው ታጣቂ ቡድኑ ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ተደርሶባቸው በእስር ቤት እንዳሉ ተሳምቷል።

 

በወራት በፊት የጥንታዊው እና በታሪካዊው ዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም አራት መነኮሳት  በግፍ መገደላቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ግድያው በ ” ሸኔ ታጣቂዎች ” መፈፀሙን መግለጿም አይዘነጋም።

በወቅቱ አንድ የገዳሙ መነኩሴ ከሟቾቹ ጋር የነበሩ ዱካቸው መጥፋቱም ሲገለጽ እንደነበር ይታወሳል።

እኚሁ መነኩሴ ግድያውን ፈጽሟል ከተባለው ታጣቂ ቡድኑ ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ተደርሶባቸው በእስር ቤት እንዳሉ ተሳምቷል።

ይህ የተሰማው ከቀናት በፊት በመንግስታዊ ቴሌቪዥን ጣቢያዎች በዝቋላ ገዳም በታጣቂዎች ስለሚደርሰው ግፍን በተመለከተ በተሰራጨ አንድ ፕሮግራም ላይ የገዳሙ አባቶች ሲናገሩ ነው።

በወቅቱ ምን ሆነ ?

የካቲት 12 /2016 ዓ/ም ከገዳሙ ከተወሰዱት እና በኃላም ለምምክር ተብለው ከተጠሩት 5 መነኮሳት አንድ መነኩሴ ሳይገደሉ በህይወት ተርፈው ወደ ገዳሙ ተመልሰዋል።

አባ ገ/ኢየሱስ ፀጋዬ ፦

” መጀመሪያውኑ መረጃውን የሚሰጥ ከኛ ውስጥ አደራጅተዋል። እነሱ ናቸው የኛን እያንዳንዱን መረጃ የሚሰጧቸው።

ይሄን እኛ አናውቅም በወቅቱ ፤ አሁንም ቢሆን ሀገር መከላከያ መጥቶ መረጃው እንዲህ እንዲህ ነው ብሎ ስልካቸውን ጠልፎ ያለውን መረጃ ከእንቅስቃሴያቸው አኳያ ነው ያወጣልን እንጂ ውስጡን አናውቅም።

እንደኛው ቆብ ያደርጋሉ፤ መናኝ ናቸው።

እነሱ ተርፈው የመጡት አባት የምንጠራጠራቸው መከላከያው በትክክል መረጃ አግኝቶባቸዋል።

እሳቸው ወደ ማታ መጡ ተባሉ ግን የሸኛቸው ሸኔ ነው እስከ ግማሽ መንገድ ከመጡ በኃላ በራቸውን ዘግተው በውጭ አስቆልፈው ተቀምጠዋል።

ማታ 2 ሰዓት ላይ ሀገር መከላከያ ሰራዊት መጡ እኚያን በአስቸኳይ መያዝ ስለነበረባቸው የት ነው ያሉት አሉ ? ሄደው ከቤታቸው ሲፈለጉ ጠፉ በውጭ ተቆልፏል ከዛ በሩ ይሰበር ተብሎ በሩን መከላከያዎቹ ሰብረው አገኟቸው በቁጥጥር ስር አዋሏቸው።

ከዛ መከላከያው እኛን የማረጋጋት ስራ ነው የሰራው። እርግጠኛ ሆኜ ምናገረው በወቅቱ ሀገር መከላከያ ባይመጣ አናድርም ነበር።

አሁንም በየጫካው ተሰማርተው ጥበቃ እያደረጉ ነው። ”

አባ ተ/መድህን ገ/መስቀል ፦

” ገንዘባችንን ፣ መሳሪያዎቻችንን በመውሰድ ባላቸው ሲስተም ከውስጣችንም ሳይቀር ከነሱ ጋር የተዋሃደ ኃይል ያለውን ንብረታችንን ሁሉ እስከማጣት ደርሰናል። መከላከያ ኃይል በመረጃ ነው ሊያወጣቸው የቻለው። ”

ገረመው ይርጋ (የሉበን ጩቃላ ወረዳ ሚሊሻ) ፦

” ይሄን ሁሉ ሲያደርጉ ብቻቸውን አይደለም። የራሳቸውን ሰው ከቤተክርስቲያን ውስጥ አሰማርተው ይህ ስራ ሲሰራ ነበር። ከህዝቡም ከነዋሪው አደራጅተው ያንን ስራ ይሰራ ነበር።

መጨረሻ ላይ እነዛ አባቶች ታግተው ሄደው አባቶችም መስእዋትነት ከፈሉ።

እነዛም ተመሳጥረው የነበሩት በጣም አደገኛ የተባለው ተይዟል። በቁጥጥር ስር የዋሉም አሉ። ”

ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ፤ ” ድሮም የሚጎዳው የውስጥ አዋቂ ነው ” ብለዋል።

” የቀረቡ መስለው ፣ አብረው የመነኑ መስለው ፣ አብረው ከገዳሙ ሰዎች ጋር በደባልነት በአስመሳይነት የሚኖሩ እንደነበሩ ጭላንጭሎች ነበሩ ይሄን ሁላችንም እናውቃለን ” ሲሉ ገልጸዋል።

በዚሁ በቀረበው ፕሮግራም ላይ የገዳሙ አባቶች ፥ ታጣቂዎቹ ከውስጥ ባላቸው ሰዎች አማካኝነት እያንዳድኑ ንብረት የት እንደሚቀመጥ በማወቅ በተደጋጋሚ ጊዜ ዝርፊያ ሲፈጽሙ እንደከረሙ ተናግረዋል።

ይህንን ለፀጥታ ኃይል ካሳወቁ ቤተክርስቲያኗን ጭምር በቦምብ እንደሚያወድሙ ሲዝቱ እንደነበር ገልጸዋል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ ፡-(@tikvahethiopia)