“ ለአጋቾቹ 700 ሺሕ ከከፈልኩ በኋላ እንደገና 400 ሺሕ ጠየቁኝ ” – በሊቢያልጃቸውየታገተባቸው አባት…..

በአዲስ አበባ ከተማ በካሜራ ማን የሥራ ዘርፍ ተሰማርቶ ይሰራ የነበረው አብርሃም አማረ የተባለ ወጣት ሕይወቱን ለመለወጥ ወደ ውጭ እየተሰደደ በነበረበት ወቅት በሊቢያ በደላሎች እንደታገተባቸው፣ አጋቾቹ ልጁን ለመልቀቅ 950 ሺሕ ብር እንደጠየቋቸው የታጋች አባት አቶ አማረ ዓለም መግለጻቸውን ከሁለት ሳምንታት በፊት ዝርዝር መረጃ አድርሰናችሁ ነበር።

የታጋቹ አባት በወቅቱ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ በሰጡት ቃል፣ “ አጋቾቹ እያሰቃዩት ነው። ዱብ እዳ ወረደብኝ። ወደ 950 ሺሕ ጠይቀዋል። ልጄ ‘በአንድ መጋዘን ወደ 200 ሰዎች ታጎርን’ ነው የሚለው ” ማለታቸው አይዘነጋም።

አሁንስ የታጋቹ ጉዳይ ከምን እንደደረሰ ? ሲል ቲክቫህ ኢትዮጵያ አቶ አማረ ዓለምን ጠይቋል እሳቸውም ፥ “ ለአጋቾቹ 700 ሺሕ ከከፈልኩ በኋላ እንደገና 400 ሺሕ ጠየቁኝ ” ብለዋል።

“ ባለፈው ጎረቤቶች፣ ወዳጅ ዘመዶች፣ በጎ አድራጊዎች ተባብረው ገንዘብ ተሰባሰበልኝ። እግዚአብሔር ይመስገን ብዬ ከታሰረበት ወጣልኝ። አሁን እንደገና ወደዚህ (ወደ ኢትዮጵያ) መመለስ አይችልም ተብሎ እንደገና 400 ሺሕ ብር ደግሞ ተጠይቀናል ” ሲሉ አክለዋል።

ከዚህ በፊትም በተገለጸው መሠረት አጋቾቹ ታጋቹን ለመልቀቅ እንዲላክላቸው ጠይቀው የነበረው 950 ሺሕ ነበር ቀንሰውላችሁ ነው 700 ሺሕ የላካችሁት ? ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ፥ ቀንሰውልላቸው እንደነበር ገልጸው፣ አሁን ከተጠየቁት 400 ሺሕ ብር ሲደመር ግን በአጠቃላይ ደላሎች የጠየቋቸው የገንዘብ መጠን ከ1 ሚሊዮን በላይ እንደሆነ አስረድተዋል።

አሁን 400 ሺሕ ብሩን ላኩ የተባሉት ለምን እንደሆነ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ፣ ‘ ልጁ ወደ ጣሊያን እንዲሻገር ‘በሚል ሊቢያ እና ጣሊያን ያሉ ደላሎች ገንዘቡን እንደጠየቋቸው፣ ልጃቸው አሁን ትሪፓሊ ከተማ ውስጥ እንደሚገኝ ፣ ገንዘቡ ካልገባ አደጋ ሊገጥመው እንደሚችል ልጃቸው ጭምር እንደነገራቸው ነው ያስረዱት።

ድጋሚ የተጠየቀውን 400 ሺህ ብር አሟልቶ ለመላክ 150 ሺሕ ብር እንደጎደላቸውም የታጋቹ አባት ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል።

የአቶ አማረን ልጅ ጨምሮ በሊቢያ ታግቶ 1.7 ሚሊዮን ብር የተጠየቀበት፣ 800 ሺሕ ብር ለአጋቾቹ በመላኩ ይለቀቃል ተብሎ እየተጠበቀ ያለውን የሀዋሳውን ታጋች የጌድዮ ሳሙኤልን ጉዳይ ከጊዜ በኋላ በዝርዝር መረጃ የምናቀርብላችሁ ይሆናል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ ፡-(@tikvahethiopia)