ለአምስተኛ ጊዜ ቃለ መሃላ የፈጸሙት ፑቲን

ቭላድሚር ፑቲን ለአምስተኛ ጊዜ ከታላቁ ክሬምሊን ቤተ መንግስት ወደ ሴንት አንድሪው የዙፋን አዳራሽ የተዘረጋውን ረዥም መንገድ በእግር ተጉዘዋል።

አዳራሹ ደርሰው ቃለ መሃላ ፈጽመው ለቀጣይ ስድስት ዓመታት የሩሲያ ፕሬዝዳንት ሆነው ሆነው መቀጠላቸውን አረጋግጠዋል።

ፕሬዝዳንት ፑቲን በስፍራው ለተሰባሰቡት ሚኒስትሮች እና ሹማምንት “አንድ እና ታላቅ ህዝብ ነን። ሁሉንም መሰናክሎች እናልፋለን፤ ሁሉንም ዕቅዶቻችንን እናሳካለን፤ እናም አብረን እናሸንፋለን” ብለዋል።

ፑቱን የቀይ ምንጣፍ ጉዞውን በተደጋጋሚ አድርገውታል ። እአአ ግንቦት 2000 ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለ ሲመታቸውን ካከናወኑበት ስነ-ስርዓት በኋላ ብዙ ነገር ተለውጧል።

በወቅቱ ፕሬዝዳንት ፑቲን “ዲሞክራሲን ለመጠበቅ እና ለማሳደግ፤ ሩሲያን የተሻለች ለማድረግ” ቃል ገብተው ነበር።

ከሃያ አራት ዓመታት በኋላ የክሬምሊኑ ቁንጮ በዩክሬን ላይ ጦርነት ከፍተዋል። ያውም ሩሲያ ላይ ከባድ ኪሳራ ያደረሰባት ጦርነት። ፕሬዚደንት ፑቲን ዴሞክራሲን ከማጎልበት ይልቅ እየገደቡት ነው። ተቺዎችን ማሰር፣ የሌሎች የመንግስት አካላትን ሚና በመገደብ ላይ አነጣጥረዋል።

“ፑቲን እራሱን እንደ ታላቁ ቭላድሚር፣ እንደ ሩሲያ ቄሳር አድርጎ ያስባል” ሲሉ የቀድሞ የዋይት ሃውስ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ፊዮና ሂል ተናግረዋል።

“የመጀመሪያዎቹን ሁለት የፕሬዚዳንትነት ዘመናቸውን ከተመለከትን ስለ ፑቲን ጥሩ ግምገማ የሚኖረን ይመስለኛል። አገሪቷን በፖለቲካ የተረጋጋች እንድትሆን አድርጓታል። የሩሲያ ኢኮኖሚ እና ስርዓት መንግስት ከቀደሙት ዓመታት ሁሉ በተሻለ ሁኔታ አፈጻጸም ነበረው።”

“ከዛሬ 10 አመት በፊት ክሪሚያን ወደ ሩሲያ ግዛትነት ከመለስ በኋላ ግን አቅጣጫው በአስደናቂ ሁኔታ ተቀየረ። እሱ እራሱን ከችግር ፈቺነት ይልቅ ወደ ኢምፔሪያሊስት እንዲቀየር አድርጎታል።”

ለአምስተኛ ጊዜ ቃለ መሃላ የፈጸሙት ፑቲን በዘውድ በአዳራሹ ውስጥ ብዙ ደጋፊዎች አሏቸው።

“ፑቲን ሩሲያን ወደ ድል እየመራው ነው” ሲሉ የሩሲያ የፓርላማ አባል ፒዮትር ቶልስቶይ ተናግረዋል።

“ድል ምንድን ነው?” የሚል ጥያቄ ቀረበላቸው።

“ድል ማለት ብሪታንያ እና ምዕራባውያን ሩሲያ ልዕለ ኃያል መሆኗን ሲገነዘቡ እና የሩሲያን ብሔራዊ ጥቅም ሲገነዘቡ ነው” ምላሽ ሰጡ።

“ምዕራባውያን ይህንን ካላደረጉስ?” ቀጣዩ ጥያቄ ነበር።

“ከዚያ በኋላ የምዕራቡ ዓለም መጨረሻ ይሆናል” ሲሉ የፓርላማው አባል ደመደሙ።

በክሬምሊን ቤተ መንግስት ውስጥ ከፕሬዚዳንት ፑቲን ትልቅ አድናቂዎች አንዱን ተገኝተዋል። የሩስያ የታችኛው ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ የሆኑት ቭያቼስላቭ ቮሎዲን ናቸው።

“ፑቲን ካለ ሩሲያ አለች፣ ፑቲን ከሌለ ሩሲያ የለችም” በሚለው ንግግራቸው ታዋቂ ሆነዋል።

“የምዕራቡ ዓለም የምትፈራርስ ደካማ ሩሲያን ማየት ይፈልጋል። ፑቲን ግን እንቅፋት ሆነባቸው” ብለዋል ቮሎዲን።

ቭላድሚር ፑቲን ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ አሜሪካ አምስት የተለያዩ ፕሬዚዳንቶች እና ብሪታንያ ደግሞ ሰባት ጠቅላይ ሚኒስትሮች ቀያይራለች።

ሩሲያን ለሩብ ምዕተ-ዓመት የሚጠጋ ጊዜ ከመሩ በኋላ በእርግጠኝነት አሻራቸውን ማሳረፍ ችለዋል። ቀደም ባሉት ጊዜያት ሰዎች ስለ “ብሬዥኔቪዝም”፣ “ጎርባቼቪዝም” ወይም “የልስኒዝም” እምብዛም አይናገሩም።

ፑቲኒዝም ግን ትልቅ ነገር ነው።

በካርኔጊ የዩሬዥያ የሩሲያ ማዕከል ባልደረባ የሆኑት አንድሬ ኮሌስኒኮቭ “በታሪካችን ውስጥ አንድ ተጨማሪ -ዝም ጨምረናል። ያም ስታሊኒዝም” ብለዋል።

“ፑቲኒዝም አንድ ተጨማሪ የስታሊኒዝም መስመር ነው እላለሁ። እሱ እንደ [ቀድሞው የሶቪየት አምባገነን መሪ] ስታሊን ነው የሚንቀሳቀሰው። ልክ እንደ ስታሊን ጊዜ ስልጣኑ በእጁ ነው። ብዙ የፖለቲካ ጭቆናዎችን መጠቀምን ይመርጣል። እንደ ስታሊን ሁሉ እሱም በህይወት እስካለ ደረስ በስልጣን ለመቆየት ዝግጁ ነው።”

ለምዕራቡ ዓለም ተግዳሮትነቱ እየጨመረ የመጣውን ፈላጭ ቆራጭ የሆነውን የሩስያ መሪ የሚያስተናግዱበት መንገድ ነው። ፑቲን ሩሲያን ታላቅነት ለመመለስ ቆርጦ የነተነሳ፤ የኒውክሌር ባለቤት … የዘመናችን ቄሳር።

“በኒውክሊየር ጦር መሳሪያ ጉዳይ ላይ ልንሠራው የምንችለው በጣም ከባድ ነገር አለ” ብለዋል ፊዮና ሂል።

“እንደ ቻይና፣ ህንድ እና ጃፓን ያሉ አንዳንድ አገራት ፑቲን በዩክሬን የኒውክሌር ጥቃት ሲገፉ በጣም ተጨንቀዋል።”

“ምናልባት ይህ በብዙ መልኩ ጨካኝ መሪ የሆነውን ቭላድሚር ፑቲንን እንዴት ልንይዘው እንደምንችል ምሳሌ የሚሆን ነገር ነው። እሱ ሊወስዳቸው ለሚፈልጋቸው አይነት ድርጊቶች የማይመች የበለጠ ገዳቢ አካባቢ መፍጠር አለብን።”

ቭላድሚር ፑቲን በመጋቢት ወር በተካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ከ 87 በመቶ በላይ ድምጽ አግኝተዋል። ይሁን እንጂ በሰፊው ነፃ እና ፍትሐዊ ተብሎ ባልታየው ምርጫ ላይ ከባድ ተፎካካሪም አልገጠማቸውም። ለሩሲያ ማዕከላዊ የምርጫ ኮሚሽን ለሊቀመንበር ኤላ ፓምፊሎቫ ጉዳዩ ቀርቦላቸው የወደዱት አይመስልም።

“ብዙ የፕሬዚዳንቱ ተቃዋሚዎች በምርጫው እንዲሳተፉ አልተፈቀደላቸውም” የሚል ሃሳብ ተነሳላቸው።

“እንዲህ አይነት ትችት የሚሰነዝሩ ሰዎች ሩሲያን አያውቁም ወይም እዚህ ለረጅም ጊዜ አልነበሩም። ሁሉም ነገር ተረት እና ውሸት ነው” ሲሉ መልሰዋል።

ቭላድሚር ፑቲንን ማግኘት የሚችሉት በታላቁ ክሬምሊን ቤተ መንግስት ብቻ አይደለም።

ከሞስኮ 112 ኪሜ ርቀት በምትገኘው ካሺራ ከተማ ውስጥ ግዙፍ የፑቲን ምስል በአንድ ሰማይ ጠቀስ ፎቅ የግድግዳ ይገኛል።

በካሺራ ውስጥ ታላቁ ቭላድሚር ይመለከትዎታል።

መንገድ ዳር አበባ በመሸጥ የሚተዳደሩት ጡረተኛዋ ቫለንቲና “እወደዋለሁ” ይላሉ።

“ፑቲን ጥሩ ሃሳቦች አሉት። ለሰዎች ብዙ ነገር ይሰራል። የእኛ ጡረታ ትልቅ አለመሆኑ እውነት ነው። ነገር ግን ሁሉንም ነገር በአንድ ጊዜ ማስተካከል አይችልም” ብለዋል።

“ወደ 25 ዓመታት ገደማ ስልጣን ላይ ቆየ እኮ” የሚል ጥያቄ ተነሳላቸው።

“ቀጥሎ (ከፑቲን በኋላ) ማን እንደሚመጣ አናውቅም” ሲሉ ቫለንቲና መለሱ።

የፑቲንን ስዕል እየተመለከተች የምታልፈው ቪክቶሪያ ደግሞ “በሩሲያ ሁላችንም አንድ አይነት አስተሳሰብ እንዲኖረን ይጠበቃል” ብላለች።

“ስለፑቲን አንድ ነገር ከተናገርኩ ባለቤቴ፡ ‘ፑቲንን እንደገና ትነቅፊና እፈታሻለሁ’ ይላል። እሱን በጣም ይወደዋል። ፑቲን ባይኖር ኖሮ ህይወታችን ኑሮ ልክ እንደ 1990ዎቹ ከባድ ይሆን ነበር ይላል።”

መንገድ ሲጓዝ የነበረው አሌክሳንደር ስለ ፕሬዝዳንቱ ያለውን አመለካከት ሲጠየቅ “ሃሳብን መግለጽ አደገኛ ሊሆን ይችላል ምንም አስተያየት የለኝም” ሲል መልስ ሰጠ።

ያናገርናቸው አብዛኛዎቹ ሰዎች የፑቲንን ፎቶ አሁንም መኖሩን እንኳን ሳያውቁ አልፈው እንደሚሄዱ ይናገራሉ። ለምደውታል።

አንድ ሰው ለዘመናት ሩሲያን መርቷል። ክሬምሊን አዲስ ሰው ማግኘቱ ጉዳይ ተስፋ ያለው አይመስልም።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ ( ቢቢሲ ዜና )