“ህወሓት የፕሪቶሪያውን ስምምነት ጥሶ አራተኛ ዙር ወረራ ፈጸመ” ሲል የአማራ ክልል ከሰሰ

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ህወሓት የፕሪቶሪያውን ስምምነት ሙሉ በሙሉ በመጣስ አራተኛ ዙር ወረራ በሕዝብ በላይ ፈጽሟል ሲል ከሰሰ።

የክልሉ መንግሥት ዛሬ የሚያዝያ 9/2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫው “ከትናንት ታሪካዊ ስህተቱ መማር የተሳነው ህወሓት የፕሪቶሪያውን ስምምነት ሙሉ በሙሉ በመጣስ ለአራተኛ ዙር ሕዝባችን ላይ ወረራ ፈፅሟል” ብሏል።

ክልሉ ይህንን ያለው ካለፈው ሳምንት ማብቂያ ጀምሮ አወዛጋቢ በሆኑት የራያ አካባቢዎች ለቀናት የዘለቀ የተኩስ ልውውጥ ከተካሄደ በኋላ በከተሞች አካባቢ የመከላከያ እና የፌደራል ፖሊስ በዙሪያቸው ደግሞ የህወሓት ታታቂዎች መግባታቸው ከተገለጸ በኋላ ነው።

የክልሉ መንግሥት ዛሬ ረቡዕ ባወጣው መግለጫ ህወሓት ወረራ የፈፀመባቸው የራያ አላማጣ፣ ራያ ባላ፣ ኦፍላ፣ ኮረም እና ዛታ መሆናቸውን በመግለጽ የክልሉ ሕዝብ፣ የፌደራል መንግሥቱ እና ዓለም አቀፍ ኅብረተሰብ ድርጊቱን እንዲያስቆሙ ጥሪ አቅርቧል።

ትናንት መግለጫ የሰጡት የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጄኔራል ታደሠ ወረደ፣ “በደቡባዊ ትግራይ እና ጸለምት ወረዳዎች” የአማራ ክልል የተቋቋሙ አስተዳደሮችን ለማፍረስ በፌዴራል መንግሥቱ እና በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር መካከል ስምምነት መደረሱን ተናግረው ነበር።

የማንነት ጥኣቄ ሲነሳባቸው የነበሩ እና በሰሜን ኢትዮጵያ የተካሄደው ጦርነት ከመጀመሩ በፊት በትግራይ ክልል ስር የነበሩ አካባቢዎች ከጦርነቱ በኋላ በአማራ ክልል ኃይሎች ቁጥጥር ስር መግባታቸው ይታወቃል።

ቀደም ሲል የፌደራል መንግሥቱ ከአወዛጋቢዎቹ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ነዋሪዎች እንዲመለሱ እና የእራሳቸውን አስተዳደር እንዲያቋቁሙ እንዲሁም በቀጣይነትም ሕዝበ ውሳኔ በማድረግ የይገባኛል ጥያቄዎቹ ምላሽ እንደሚያገኙ ገልጾ ነበር።

ጄኔራል ታደሰ ወረደ በሰጡት መግለጫ ላይ በአካባቢዎቹ የሚንቀሳቀሱ የታጣቂ ቡድኖች ትጥቅ እንዲፈቱ እንደሚደረግ ጠቅሰው በአወዛጋቢዎቹ አካባቢዎች ሕዝበ ውሳኔ ይካሄዳል የሚለው የፌደራል መንግሥትን ውሳኔ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አቋም እንዳልሆነ አመልክተዋል።

ወረራ ተፈጽሞብኛል ያለው የአማራ ክልል መንግሥት በመግለጫው አወዛጋቢ ቦታዎቹን በተመለከተ በፌደራል መንግሥቱ አማካይነት ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር ውይይት ለማድረግ በርካታ ሙከራዎች የተደረጉ ቢሆንም “ህወሓት ይህን የሰላም አማራጭ ወደ ጎን በመተው የማንነት ጥያቄ ያለባቸውን የራያ አላማጣ፣ ራያ ባላ፣ ኦፍላ፣ ኮረም እና ዛታ አካባቢዎች” መውረሩን ገልጿል።

ስለዚህም ህወሓት ደም አፋሳሽ ጦርነት ለማድረግ ከመሞከር እንዲታቀብ እና የፕሪቶሪያውን ስምምነት ሙሉ በሙሉ በማክበር በወረራ ከያዛቸው አካባቢዎች በአስቸኳይ ለቆ እንዲወጣ ጠይቋል።

“ይህ የማይሆን ከሆነ የአማራ ክልል መንግሥት እና ሕዝብ ከሌሎቹ ወንድም እና እህት ኢትዮጵያውያን ጋር በጋራ በመሆን አገርን ከማፍረስ መታደግና ሕዝባችንንም ከጥቃት ለመከላከል የምንገደድ መሆኑን ለማሳወቅ እንወዳለን” ሲል አስጠንቅቋል።

ክልሉ በመግለጫው የፕሪቶሪያውን ስምምነት ሲያፈርስ ቆይቷል ያለው ህወሓት “በሙሉ አቅሙ ወደ ጦርነት ገብቷል” በማለት የፌደራል መንግሥቱ ቡድኑ “በአጭር ጊዜ ከወረራቸው አካባቢዎች ለቆ እንዲወጣ በማድረግ ሕዝባችንን ከጥፋት መታደግ እና የአገራችንን ሉዓላዊነት ማስከበር ይገባል” ሲል ጥሪ አቅርቧል።

አማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በተመሳሳይ ትናንት ባወጣው መግለጫ ህወሓት በራያ በኩል “ቀጥተኛ የሆነ ጥቃት” በመክፈት “አራተኛ ዙር ወረራ ፈጽሟል” ሲል ከስሷል።

አብን በመግለጫው፤ “ፌዴራሉ መንግሥት እና የአማራ ክልል መንግሥት በሕዝባችን ላይ እየተፈጸመ የሚገኘውን ወረራ በአስቸኳይ እንዲያስቆሙ አበክረን እንጠይቃለን” ብሏል። “በሁሉም አካባቢዎች” የሚገኘው የአማራ ሕዝብ ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጋር በመቀናጀት ጥቃቱን እንዲመክት ጥሪ አቅርቧል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአማራ ክልል መግለጫ ከማውጣቱ አንድ ቀን ቀደም ብሎ የትግራይ ክልላዊ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ በትግራይ እና አማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች የሚሰተዋለው ግጭት በትግራይ እና በአማራ ወይም በትግራይ እና በፌደራል መንግሥቱ መካከል የተፈጠረ አይደለም ብለው ነበር።

ጌታቸው ረዳ በሁለቱ ክልሎች መካከል የይገባኛል ጥያቄ የሚነሳባቸው አካባቢዎችን የተመለከተ ንግግር በአዲስ አበባ እየተካሄደ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።

በአካባቢዎቹ የሚታየው ሁኔታ የፕሪቶሪያ ስምምነት እንዲተገበር የማይፈልጉ “የስምምነቱ ጠላቶች ሥራ” መሆኑን በመልዕክታቸው አስፍረዋል። “ፀረ ፕሪቶሪያ” ስምምነት የሆኑ “ቅርብ እና ሩቅ የሚገኙ” አካላት “የጦርነት ቅስቀሳ” ቢኖርም ብቸኛው መንገድ “ሰላም” እና “ንግግር” መሆኑን አቶ ጌታቸው ጠቅሰዋል።

የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ በአማራ ክልል ስር የገቡት አወዛጋቢ አካባቢዎች ጉዳይ መፍትሔ የሚያገኘው በሕዝበ ውሳኔ እንደሆነ የፌደራል መንግሥት መግለፁ ይታወሳል። ጉዳዩን ለመፍታትም ከፌደራል መንግሥት እንዲሁም ሁለቱ ክልሎች ከፍተኛ አመራሮች ያሉበት ዐቢይ ኮሚቴ ሥራ ላይ መሆኑን የፌደራል መንግሥት አስታውቆ ነበር።

ከሁለት ሳምንት በፊት ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ሚኒስትር ዶ/ር ለገሰ ቱሉ፤ “በአማራ አዋሳኝ አካባቢዎች” ላይ “በትግራይ በኩል” የሚታየው “አዝማሚያ”፤ የፕሪቶሪያውን ስምምነት የሚጥስ” እንደሆነ ተናግረው ነበር።

ዶ/ር ለገሰ፤ “ወሰንን በኃይል እናስከብራለን” የሚል አካሄድ “የትግራይ ሕዝብን ለሌላኛው ዙር ስቃይ እና እንግልት የሚዳርግ ነው” ሲሉም በዚህ መግለጫቸው አሳስበው ነበር።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ ( ቢቢሲ ዜና )