ህንዳዊቷ ተዋናይት ስጋ ስትበላ የምትታይበት ፊልም ከቀናት ቆይታ በኋላ ከኔትፍሊክስ ወረደ

“የሂንዱ እምነትን አንቋሿል” የተባለው የህንድ ፊልም ኔትፍሊክስ ከተሰኘው የፊልም ማሰራጫ እንዲወርድ ተደረገ።

ኔትፍሊክስ ፊልሙን ከቋቱ ያወረደው ከቀናት ቆይታ በኋላ ነው።

ኔትፍሊክስ እንዳለው በታሚል ቋንቋ የተሠራው አናፑራኒ [የምግብ አምላክ] የተሰኘው ፊልም የወረደው “በአዘጋጆቹ ጥያቄ” መሠረት ነው።

ተዋናይት ናያንታራ የምትሠራበት ፊልም አንዲት የሂንዱ ብራህሚን ሴት ሼፍ ለመሆን ስትጣጣር ያሳያል።

ገፀ-ባሕሪዋ ከቤተሰቦቿ እምነት ውጭ ስጋ ስትበላ እንዲሁም ስታበስል ትታያለች።

በርካታ ብራህሚኖች ጥብቅ በሆነው እምነታቸው መሠረት ስጋ አይበሉም።

ወግ አጥባቂ የሂንዱ እምነት ድርጅቶች ይህንን ጨምሮ ሌሎች የፊልሙ ትዕይንቶችን በመቃወም ድምፃቸውን አሰምተዋል።

በአንዱ የፊልሙ ትዕይትን ተዋናይቷ ናማዝ ወይም የሙስሊም ፀሎት አድርጋ ብሪያኒ የተሰኘውን ምግብ ስታበስል ትታያለች።

አንዳንድ የሂንዱ እምነት ተከታዮች አንድ ሙስሊም ገፀ-ባሕርይ የሂንዱ አምላክ የሆነው ራም ስጋ ይበላል ሲል መስማታቸው አስቆጥቷቸዋል።

የፊልሙ አዘጋጆች እስካሁን ስለተፈጠረው ነገር ሰጡት አስተያየት የለም።

በማዲያ ፕራዴሽ ግዛት በናያንታራ እና ሌሎች ሁለት ከፊለሙ ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ ግለሰቦች ላይ የፖሊስ መዝገብ መከፈቱ ተሰምቷል።

በ2021 አማዞን ፕራይም በተሰኘው ማሰራጫ የተላለፈው ታንዳቭ የተሰኘው ፊልም አዘጋጆች የደረሰባቸውን ወቀሳ ተከትሎ ይቅርታ መጠየቃቸው አይዘነጋም።

በሲኒማዎች በአውሮፓውያኑ ታኅሣሥ 1 የተለቀቀው አናፑራኒ ከሀያሲያን የተደበላለቀ አስተያየት አስተናግዷል።

ግማሹ ፊልሙ ከአንድ ወግ አጥባቂ ቤተሰብ የመጣች ሴት ሕልሟን ስትከተል ማሳየቱን ቢወዱትም ሌሎች ደግሞ ፊልም “ያልበሰለ” ሲሉ ተችተውታል።

ፊልሞች ለሕዝብ ከመብቃታቸው በፊት ሳንሱር የሚሠራው የህንድ ማዕከላዊ የፊልም ሰርቲፊኬት ቦርድ ፊልሙ ይለፍ ብሎት ነበር።

ነገር ግን ፊልሙ አጨቃጫቂ ሆኖ የተገኘው በኔትፍሊክስ ተሰራጭቶ በርካቶች ከተመለከቱት በኋላ ነው።

የወግ አጥባቂው ቪሽዋ ሂንዱ ፓሪሻድ አባላት ሙምባይ ከሚገኘው የኔትፍሊክስ ቢሮ ውጭ ተቃውሞ ማሰማታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

የፊልሙ አዘጋጆች የተነሳውን ውዝግብ በተመለከት አስተያየት እንደሚሰጡና ፊልሙ አርትዖት እስኪደረግለት ድረስ ከኔትፍሊክስ ወርዶ እንደሚቆይ ተዘግቧል።

አንዳንዶች ፊልሙ ከኔትፍሊክ በመውረዱ ደስታቸውን ቢገልጡም ሌሎች ደግሞ ይህ አደገኛ ምሳሌ ነው ሲሉ ይከራከራሉ።

ምንጭ ( ቢቢሲ ዜና )